ምዕራፍ 1
1
እኔ የሐካልያ ልጅ ነህምያ ነኝ፡፡ ንጉስ አርጤክስስ የፋርስን መንግስት መግዛት በጀመረበት በሃያኛው አመት፣ ካሴሉ በተባለው ወር፤ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሼ ያደረግሁትን ይህን ነገር ጻፍሁ፡፡ እኔም በፋርስ ዋና ከተማ በሱሳ ነበርሁ፡፡
2
ወንድሜ አናኒ እኔን ለማየት መጣ፡፡ እርሱና ሌሎች ጥቂት ሰዎች ከይሁዳ መጥተው ነበር፡፡ ከባቢሎን ምርኮ ስላመለጡ ጥቂት አይሁዶች፣ እና ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ ጥያቄዎችን ጠየቅኳቸው፡፡
3
እነርሱም እንዲህ አሉኝ፣ “ከምርኮ ያመለጡት አይሁዶች በዚያ በታላቅ መከራ እና ውርደት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ የከተማዋ ቅጥሮች በብዙ ስፍራዎች ተገፍተው ስለወደቁ ጠላት በቀላሉ ይገባባታል፣ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን የከተማዋ በሮች ሙሉ በሙሉ በእሳት ተቃጥለዋል፡፡”
4
ይህንን በሰማሁ ጊዜ፣ ተቀምጬ አለቀስኩ፡፡ ለብዙ ቀናት በሰማይ ወዳለው አምላክ በለቅሶ ጾምኩ ጸለይኩ፡፡
5
እንዲህ ስል ጸለይኩ፣ “ያህዌ፣ አንተ በሰማይ ያለህ አምላክ ነህ፡፡ አንተ ታላቅና አስደናቂ አምላክ ነህ፣ ለሚወዱህና ህግጋትህንና ትዕዛዛትህን ለሚጠብቁ ሁሉ የተቀደሰውን አብሮነትህንና ቃልኪዳንህን ትጠብቃለህ፡፡
6
እባክህ አሁን ወደ እኔ ተመልከት ወደ ጸሎቴም አድምጥ፡፡ በቀንና በለሊት ለህዝብህ ለእስራኤል እጸልያለሁ፡፡ ኃጢአት መስራታችንን እናዘዛለሁ፡፡ እኔና ቤተሰቤ ጭምር አንተን በድለናል፡፡
7
በጣም ክፉ አድርገናል፡፡ ከብዙ አመታት አስቀድሞ ባሪያህ ሙሴ አንተ እናደርገው ዘንድ ያዘዝከውን ህግጋትና ስርዓቶች ሰጥቶናል፣ እኛ ግን ህግጋትህን አልጠበቅንም፡፡
8
እባክህ ለአገልጋይህ ለሙሴ የተናገርከውን አስብ፡፡ እንዲህ ብለሃል፣ ‘በፊቴ በታማኝነት እና በመታዘዝ ባትመላለሱ በአገራት መሃል እበትናችኋለሁ፡፡
9
ነገር ግን ወደ እኔ ብትመለሱ እና ትዕዛዞቼን ብትጠብቁ፣ ወደ ሩቅ ሥፍራዎች ብትጋዙም እንኳን፣ ሁላችሁንም ሰብስቤ የእኔን ታላቅነትና ክብር ወደማሳያችሁ ወደዚህ ስፍራ እመልሳችኋለሁ፡፡
10
እኛ የአንተ አገልጋዮች ነን፡፡ በታላቁ ሀይልህ ከባርነት ነጻ ያወጣኸን ህዝብ ነን፡፡ አንተ ያንን ያደረግከው ማድረግ የምትፈልገውን ሁሉ ማድረግ ስለምትችል ነው፡፡
11
ያህዌ፣እባክህ የእኔን የአገልጋይህን ፀሎት ስማ፡፡ እባክህ በማንነትህና በስራህ አንተን ሲያከብሩ፣ ታላቅ ሀሴት የሚያደርጉትን የህዝብህን ሁሉ ጸሎት ስማ፡፡ ወደ ንጉሱ ፊት ስቀርብ መከናወንን እንድትሰጠኝ እጸልያለሁ፤ ለንጉሱ ጥያቄዬን ሳቀርብ ህይወቴ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ ጠብቃት፡፡ ምህረትህ ይከተለኝ፡፡”
እኔ ለንጉሱ እጅግ ከታመኑት አገልጋዮች አንዱ ሆኜ አገለግል ነበር፡፡