ምዕራፍ 9

1 ኢየሱስም እውነት እላችኋለሁ፣ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶቹ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል መምጣቷን ሳያዩ የማይሞቱ አሉ አላቸው፡፡ 2 ከስድስት ቀን በኋላም ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ለብቻቸው ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ላይ አመጣቸው፡፡ 3 በፊታቸውም ተለወጠባቸው፤ ልብሱም አጣቢ በምድር ላይ ሊያነጻው እስከማይችል ድረስ ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ፡፡ 4 ሙሴና ኤልያስ ታዩአቸው፤ ከኢየሱስ ጋርም ይነጋገሩ ነበር፡፡ 5 ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ረቡኒ! በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴና አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳሶችን እንሥራ አለው፡፡ 6 እጅግ ፈርተው ስለነበረ የሚመልሰውን አያውቅም ነበር፡፡ 7 ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፣ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ፡፡ 8 ድንገት ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ከእነርሱ ጋር ሌላ ማንንም አላዩም፡፡ 9 ከተራራው ሲወርዱ ሳሉም ይህንን ያዩትን ነገር ሁሉ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሳ ድረስ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፡፡ 10 እነርሱም ቃሉን ይዘው ከሙታን መነሳት ማለት ምን ማለት ነው ተባባሉ፡፡ 11 እነርሱም ጸሐፍት አስቀድሞ ኤልያስ መምጣት አለበት የሚሉት ለምንድነው ብለው ጠየቁት፡፡ 12 ኢየሱስም ኤልያስማ በርግጥ አስቀድሞ ይመጣል፤ ሁሉንም ነገር ያስተካክላል፡፡ ስለ ሰው ልጅ ብዙ መከራ እንዲቀበልና እንዲጣል የተጻፈው ታዲያ እንዴት ይሆናል? 13 እኔ ግን እላችኋለሁ! ኤልያስ መጥቷል፤ ስለ እርሱም አንደተጻፈው የወደዱትን አደረጉበት፡፡ 14 ወደ ደቀመዛሙርቱ በመጡ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ከበዋቸው ጸሓፍትም ሲጠይቋቸው ተመለከቱ፡፡ 15 ወዲያው ሕዝቡ ሁሉ ኢየሱስን ባዩት ጊዜ እጅግ ተገርመው ወደ እርሱ በመሮጥ ሰላምታ ሰጡት፡፡ 16 እርሱም ስለምንድነው የምትጠይቋቸው? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ 17 ከሕዝቡም መሐል አንዱ መምህር ሆይ! ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወዳንተ አመጣሁት፡፡ 18 በሚወስደው ቦታ ሁሉ ይጥለውና አረፋ ያስደፍቀዋል፣ ጥርሱን ያንቀጫቅጭና ያደርቀዋል፡፡ እንዲያወጡት ደቀመዛሙርትህን ጠየቅኳቸው፣ እነርሱም አልቻሉም፡፡ 19 ኢየሱስም መልሶ እናንተ የማታምኑ ትውልዶች እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሳችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው፡፡ 20 ወደ እርሱም አመጡለት፤ ባየውም ጊዜ ወዲያው መንፈሱ በምድር ላይ በኃይል ጥሎ እያንፈራገጠ አረፋ አስደፈቀው፡፡ 21 ኢየሱስም የልጁን አባት ይህ ከያዘው ምን ያህል ጊዜ ሆነው? ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም ከሕጻንነቱ ጀምሮ ነው፡፡ 22 ብዙ ጊዜ ሊያጠፋው በውሃና በእሳት ላይ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ እዘንልንና እርዳን አለው፡፡ 23 ኢየሱስም የሚቻልህ ከሆነ አልክን ለሚያምን ሁሉም ነገር ይቻላል አለው፡፡ 24 ወዲያው የልጁ አባት ጮኸና አምናለሁ፣ እንዳምንም እርዳኝ አለው፡፡ 25 ኢየሱስ ሕዝቡ እየሮጠ ሲመጣ ተመልክቶ እርኩሱን መንፈስ አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ ከእርሱ እንድትወጣ ተመልሰህም እንዳትገባበት አዝሃለሁ ብሎ ገሰጸው፡፡ 26 መንፈሱም ካንፈራገጠው በኋላ ጮኾ ወጣ፡፡ ብዙዎች ሞተ እስኪሉ ድረስም እንደ ሞተ ሰው ሆነ፡፡ 27 ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሳው፤ እርሱም ተነሣ፡፡ 28 ወደ ቤት በገቡ ጊዜም ደቀመዛሙርቱ እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድነው? ብለው ለብቻው ጠየቁት፡፡ 29 ኢየሱስም እንዲህ ዓይነቱ ወገን በጸሎት ካልሆነ በስተቀር አይወጣም አላቸው፡፡ 30 ከዚያም ወጥተው በገሊላ በኩል አለፉ፤ በዚያ መሆኑን ማንም እንዲያውቅ አይፈልግም ነበር፡፡ 31 ደቀመዛሙርቱንም እንዲህ ሲል አስተማራቸው፤ የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ታልፎ ይሰጣል፣ ይገድሉታልም፣ ከተገደለ ከሶስት ቀን በኋላም ይነሣል አላቸው፡፡ 32 ነገር ግን የተናገራቸውን አላስተዋሉም፤ እንዳይጠይቁትም ፈርተው ነበር፡፡ 33 ወደ ቅፍርናሆም መጡ፤ በቤት ሳሉም መንገድ ላይ ስለምን ጉዳይ ነበር የምትነጋገሩት ብሎ ደቀመዛሙርቱን ጠየቃቸው፡፡ 34 ከእነርሱ ማን ይበልጥ እንደሆነ ተከራክረው ነበርና ዝም አሉ፡፡ 35 ተቀምጦም አሥራ ሁለቱን ጠራቸው፣ እንዲህም አላቸው፣ ከእናንተ የመጀመሪያ ሊሆን የሚወድ የሁሉ መጨረሻና አገልጋይ ይሁን፤ 36 ትንሽ ልጅ በመካከላቸው አቁሞና አቅፎት እንዲህ አላቸው፤ 37 ማንም እንደዚህ ካሉት ታናናሽ ልጆች አንዱን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔንም የሚቀበል የሚቀበለው የላከኝን ነው እንጂ እኔን አይደለም፡፡ 38 ዮሐንስም መምህር ሆይ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያስወጣ አየነው፤ ስለማይከተለንም ከለከልነው አለው፡፡ 39 ኢየሱስ ግን በስሜ ተአምራትን አድርጎ ፈጥኖ በእኔ ላይ ክፉ ሊናገር የሚችል የለምና አትከልክሉት፤ 40 የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው አለው፡፡ 41 እውነት እላችኋለሁ የክርስቶስ በመሆናችሁ ምክንያት አንድ ብርጭቆ ውሃ እንድትጠጡ የሚሰጣችሁ ዋጋውን አያጣም፡፡ 42 በእኔ ከሚያምኑ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከእምነቱ የሚያስት ሰው ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታሥሮ በጥልቅ ባህር ላይ ቢጣል ይሻለው ነበር፡፡ 43 እጅህ ለመሰናከልህ ምክንያት የምትሆን ከሆነ ቆርጠህ ጣላት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ እሳቱ ወደማይጠፋበት ወደ ሲዖል ከምትሔድ አካልህ ጎሎ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃልና፡፡ 44 45 እግርህ ለመሰናከልህ ምክንያት የሚሆን ከሆነ ቆርጠህ ጣለው፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ሲዖል ወደ እሳቱ ከምትጣል አንድ እግር ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል፡፡ 46 47 ዐይንህ ለመሰናከልህ ምክንያት የምትሆን ከሆነ አውጥተህ ጣላት፤ 48 ሁለት ዐይን ኖሮህ ትሉ ወደማይሞትበት፣ እሳቱ ወደማይጠፋበት ከምትገባ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ብትገባ ይሻልሃል፡፡ 49 እያንዳንዱ ሰው በእሳት ይቀመማል፡፡ 50 ጨው መልካም ነው፤ የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ግን ምን ታደርጉታላችሁ? በእያንዳንዳችሁ ሕይወት የጨውነት ጣዕም ይኑርባችሁ! እርስ በርሳችሁም በሰላም ኑሩ፡፡