1 ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታም ሰዎች በመባ መሰብሰቢያ ሣጥን ውስጥ ገንዘብ ሲጨምሩ አየ። 2 አንዲት ድኻ መበለት ደግሞ ሁለት ሳንቲሞችን ስትጨምር አየ። 3 ስለዚህ እንዲህ አለ፣ "እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉም የበለጠ ሰጠች። 4 እነዚህ ሁሉ የሰጡት ስጦታ ከተትረፈረፈ ሀብታቸው ነው። ይህች መበለት ግን በድኽነቷ መተዳደሪያዋን ሁሉ ሰጠች።" 5 አንዳንዶች ቤተ መቅደሱ በተዋቡ ድንጋዮች እንዴት እንዳማረና እንዳጌጠ ሲናገሩ ሰምቶ እንዲህ አለ፣ 6 "እነዚህ የምታዩአቸው ነገሮች፣ እንዲህ እንደተነባበሩ የማይቆዩበትና የሚፈራርሱበት ጊዜ ይመጣል" አለ። 7 ስለዚህ፣ "መምህር ሆይ፣ እነዚህ ነገሮች የሚሆኑት መቼ ነው? እነዚህ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ምልክቱስ ምንድን ነው?" በማለት ጠየቁት። 8 ኢየሱስ፣ "እንዳትስቱ ተጠንቀቁ። ምክንያቱም ብዙዎች 'እኔ ኢየሱስ ነኝ፣ ደግሞም 'ጊዜው አሁን ነው' እያሉ በስሜ ይመጣሉ። አትከተሏቸው። 9 ስለ ጦርነቶችና ሁከቶች ስትሰሙ አትሸበሩ፣ እነዚህ ነገሮች አስቀድመው መፈጸም ይኖርባቸዋል፣ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም" ብሎ መለሰ። 10 ከዚያም እንዲህ አላቸው፣ "ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሣል፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል። 11 ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፣ ደግሞም በተለያዩ ቦታዎች ራብና ቸነፈር ይከሠታል። አስፈሪ ሁነቶችና ታላላቅ ምልክቶች ከሰማይ ይገለጣሉ። 12 ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች አስቀድሞ እናንተን ይይዟችኋል፣ ያሳድዷችኋል፣ ለምኩራቦችና ለወህኒ ቤቶች አሳልፈው በመስጠት ስለ ስሜ በገዦችና በነገሥታት ፊት ያቆሟችኋል። 13 ይህም ለእናንተ ለመመስከር ዕድልን ይሰጣችኋል። 14 ስለዚህ፣ አስቀድማችሁ ምን መከላከያ እናቀርባለን በማለት አትናወጡ፣ 15 ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ጠላቶቻችሁ ሊቋቋሙትና ሊቃወሙት የማይችሉትን ቃልና ጥበብ እሰጣችኋለሁ። 16 ነገር ግን በወላጆች፣ በወንደሞች፣ በዘመዶችና በጓደኞች ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ፣ ከእናንተም አንዳንዶቹን ይገድላሉ። 17 በስሜ ምክንያት በሰው ሁሉ ትጠላላችሁ። 18 ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጒር አንዲቱ እንኳ አትጠፋም። 19 በትዕግሥታችሁም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ። 20 ኢየሩሳሌም በሠራዊት ተከብባ ስታዩ ጥፋቷ መቃረቡን እወቁ። 21 በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፣ በከተማይቱ መካከል ያሉትም ለቀው ይሂዱ፣ በገጠር ያሉት ደግሞ ወደ ከተማይቱ አይግቡ። 22 የተጻፈው እንዲፈጸም እነዚህ ጊዜያት የበቀል ጊዜያት ናቸውና። 23 በእነዚያ ቀኖች ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! በምድሪቱ ላይ ታላቅ መከራ፣ በዚህ ሕዝብም ላይ ቊጣ ይወርዳል። 24 በሰይፍም ስለት ይወድቃሉ፤ ወደ ተለያዩ ሕዝቦች ሁሉ ምርኮኞች ተደርገው ይወሰዳሉ፤ የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ፣ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች። 25 በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ምልክቶች ይታያሉ። በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ከባሕርና ከማዕበል ድምፅ የተነሣ ተስፋ በመቊረጥ ይጨነቃሉ። 26 ከፍርሃትና በዓለም ላይ ሊከሰቱ ያሉትን ነገሮች ከመሥጋት የተነሣ የሚዝሉ ሰዎችም ይኖራሉ። ምክንያቱም የሰማያት ኅይላት ይናወጣሉና። 27 ከዚያም የሰው ልጅ በኅይልና በታላቅ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28 ነገር ግን እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ፣ መዳናችሁ ስለ ቀረበ ንቁ፣ ቀና ብላችሁ ተመልከቱ። 29 ኢየሱስ አንድ ምሳሌ ነገራቸው፤ “የበለስ ዛፍና ሌሎች ዛፎችን ተመልከቱ። 30 ቀንበጥ ሲያወጡ፣ በጋ እንደተቃረበ ታውቃላችሁ። 31 ልክ እንደዚሁም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። 32 እውነቱን እነግራችኋለሁ፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከመፈጸማቸው በፊት ይህ ትውልድ አያልፍም። 33 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም። 34 ልቅ በሆነ አኗኗር፣ በስካርና በጭንቀት ልባችሁ እንዳይከብድ ተጠንቀቁ። ምክንያቱም ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይመጣባችኋል። 35 በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይም ይመጣባቸዋል። 36 ነገር ግን ከሚከሠቱት ከአነዚህ ነገሮች ሁሉ እንድታመልጡና በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትበረቱ ሁልጊዜ ነቅታችሁ ጸልዩ። 37 ስለዚህ ኢየሱስ በየቀኑ በቤተ መቅደስ ያስተምር፣ ሌሊቱን ደግሞ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ እየወጣ ያሳልፍ ነበር። 38 በቤተ መቅደስም ሲያስተምር ሰዎች ሁሉ ሊሰሙት በማለዳ ይመጡ ነበር።