ምዕራፍ 1

1 ብዙዎች በእኛ ዘንድ ስለተፈጸሙት ጉዳዮች ታሪኩን በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ሞክረዋል፣ 2 ይህም የዓይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት በመጀመሪያ ለእኛ ባስተላለፉልን መሠረት ነበር፡፡ 3 ስለሆነም፣ እጅግ የተከበርክ ቴዎፍሎስ ሆይ፣ እኔም የእነዚህን ነገሮች ሂደት ከመጀመሪያው በትክክል ከመረመርኩ በኋላ፣ በቅደም ተከተላቸው መጻፍ መልካም መስሎ ታየኝ፡፡ 4 ይህንንም ያደረግሁት ስለ ተማርኸው ነገር እውነቱን ታውቅ ዘንድ ነው፡፡ 5 በይሁዳ ገዢ፣ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፡፡ ሚስቱም ከአሮን ልጆች የነበረችና ስሟም ኤልሳቤጥ የሚባል ነበር፡፡ 6 ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፣ የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ትእዛዛት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየጠበቁ ይኖሩ ነበር፡፡ 7 ነገር ግን ኤልሳቤጥ መካን ስለነበረች ልጅ አልነበራቸውም፣ በዚህ ጊዜ ደግሞ ሁለቱም አርጅተው ነበር፡፡ 8 በዚህን ጊዜ፣ ዘካርያስ በክፍሉ ተራ የክህነት አገልግሎቱን እየፈጸመ በእግዚአብሔር ፊት የሚሆንበት ጊዜ ደረሰ፡፡ 9 የትኛው ካህን እንደሚያገለግል ለመምረጥ በሚፈጸመው ልምድ መሠረት፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ዕጣ ደረሰው፡፡ 10 እርሱ ዕጣን በሚያጥንበት ወቅት፣ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ይጸልይ ነበር፡፡ 11 በዚህን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና በዕጣኑ መሠዊያ በስተቀኝ ቆመ፡፡ 12 ዘካርያስ በተመለከተው ጊዜ ደነገጠ፣ ፍርሃትም በእርሱ ላይ ወደቀ፡፡ 13 ነገር ግን መልአኩ፣ “ጸሎትህ ተሰምቶአልና ዘካርያስ ሆይ፣ አትፍራ፡፡ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፡፡ 14 ሐሴትና ደስታ ይሆንልሃል፣ ብዙዎችም በእርሱ መወለድ ሐሴት ያደርጋሉ፡፡ 15 በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና፣ ወይን ጠጅ ወይም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል፡፡ 16 ከእስራኤል ሕዝብም ብዙዎቹ ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመለሳሉ፡፡ 17 በእግዚአብሔርም ፊት በኤልያስ መንፈስና ኃይል ይመላለሳል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው የማይታዘዙት በጻድቃን ጥበብ ይሄዱ ዘንድ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች ለመመለስና የተዘጋጁትን ሕዝብ ለእግዚአብሔር ያዘጋጅ ዘንድ ነው” አለው፡፡ 18 ዘካርያስም፣ “እኔ ያረጀሁ በመሆኔና ሚስቴም ዕድሜዋ የገፋ በመሆኑ፣ ይህንን እንዴት ማወቅ እችላለሁ?” አለ፤ 19 መልአኩም፣ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንን የምሥራች እነግርህ ዘንድ ተልኬያለሁ፡፡ 20 እነሆ፣ እነዚህ ነገሮች እስኪፈጸሙ ድረስ ጸጥ ትላለህ፣ መናገርም አትችልም፡፡ ይህም የሚሆነው በትክክለኛው ጊዜ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንክ ነው፡፡” 21 በዚህን ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስን እየተጠባበቁ ነበር፣ ለረጅም ጊዜ በቤተ መቅደስ በመቆየቱም ተደነቁ፡፡ 22 በወጣ ጊዜ ግን ሊያነጋግራቸው አልቻለም፤ እነርሱም በቤተ መቅደስ በነበረበት ጊዜ ራእይ እንደ ተገለጠለት ተገነዘቡ፡፡ ለእነርሱ ምልክት ብቻ እየሰጣቸው ጸጥ ብሎ ቆየ፡፡ 23 የአገልግሎቱም ወቅት እንዳበቃ ወደ ቤቱ ለመመለስ ተነሣ፡፡ 24 ከዚህም ወቅት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፣ እንደዚህም አለች፣ 25 “በሕዝብ ዘንድ የነበረብኝን ነቀፌታ ለማስወገድ ብሎ በሞገስ ተመልክቶኝ እግዚአብሔር ለእኔ ያደረገልኝ ይህንን ነው፡፡” 26 ስድስት ወሯ በነበረ ጊዜ መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደተባለች የገሊላ ከተማ ተላከ፡፡ 27 የተላከውም ዮሴፍ ለተባለ ከዳዊት ነገድ ለሆነ ሰው ወደ ታጨች አንዲት ድንግል ነበር፡፡ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር፡፡ 28 ወደ እርሷም መጣና እንደዚህ አላት፣ “እጅግ የተከበርሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፡፡” 29 እርሷ ግን በንግግሩ በጣም ግራ ተጋባች፣ ምን ዓይነት ሰላምታ ሊሆን እንደሚችልም በማሰብ ተደነቀች፡፡ 30 መልአኩም፣ “ማርያም ሆይ፤ አትፍሪ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻል፤ 31 እነሆ፣ ፅንስ በማሕፀንሽ ውስጥ ይፀነሳል፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡ ስሙንም ‘ኢየሱስ’ ትይዋለሽ፡፡ 32 እርሱም ታላቅ ይሆናል፣ የልዑልም ልጅ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ 33 በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፣ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፡፡" 34 ማርያምም ለመልአኩ፣ “ከማንም ወንድ ጋር ተኝቼ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው፡፡ 35 መልአኩም እንደዚህ በማለት መለሰላት፣ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑል ኃይልም በአንቺ ላይ ያርፋል፤ ከዚህ የተነሣም የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡ 36 እነሆ፣ ዘመድሽም ኤልሳቤጥ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን ትባል ለነበረችው ለእርሷ ይህ ስድስተኛ ወሯ ነው፡፡ 37 ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም ነገር የለምና፡፡” 38 ማርያምም፣ “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፡፡” ከዚያ በኋላም መልአኩ ትቷት ሄደ፡፡ 39 ከዚያ በኋላ፣ ማርያም ተነሥታ በእነዚያ ቀናት በኮረብታማው አገር በይሁዳ ወዳለች ወደ አንዲት ከተማ በፍጥነት ሄደች፡፡ 40 ወደ ዘካርያስም ቤት ሄደችና ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበችላት፡፡ 41 ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ እንደዚህ ሆነ፣ በማሕፀኗ ያለው ፅንስ ዘለለ፣ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፡፡ 42 ድምፅዋን ከፍ በማድረግ ጮክ ብላ፣ “ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ፣ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ 43 የጌታዬ እናት ወደ እኔ እንድትመጣ ይህ ለምን ሆነ? 44 እነሆ፣ የሰላምታሽ ድምፅ ወደ ጆሮዬ በመጣ ጊዜ በማሕፀኔ ውስጥ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ፡፡ 45 ከጌታ የተነገሩላት ነገሮች እንደሚፈጸሙ የምታምን እነሆ እርሷ የተባረከች ናት፡፡” 46 ከጌታ የተነገሩላት ነገሮች እንደሚፈጸሙ የምታምን እነሆ እርሷ የተባረከች ናት፡፡” 46. ማርያምም፣ “ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፣ 47 መንፈሴም በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር ሐሴት ታደርጋለች፡፡ 48 የሴት ባሪያውን ውርደት ተመልክቶአልና፡፡ እነሆ፣ ከዚህ በኋላ ትውልድ ሁሉ የተባረከች ይሉኛል፡፡ 49 ብርቱ የሆነ እርሱ ለእኔ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፣ ስሙም ቅዱስ ነው፡፡ 50 ለሚያከብሩት ምሕረቱ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው፡፡ 51 በክንዱ ብርታትን ገልጾአል፣ ስለ ልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፡፡ 52 ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፣ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓቸዋል፡፡ 53 የተራቡትን በመልካም ነገር አጥግቧቸዋል፣ ባለጠጎችን ግን ባዶአቸውን ሰድዷቸዋል፡፡ 54 ምሕረት ማድረጉን ያስታውስ ዘንድ ለባሪያው ለእስራኤል ረድኤቱን ልኮለታል፣ 55 ይህንንም ያደረገው (ለአባቶቻችን እንደተናገረው) ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም፡፡” 56 ማርያም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወራት ያህል ተቀመጠች፣ ከዚያ በኋላም ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ 57 በዚያን ጊዜ ኤልሳቤጥ የምትወልድበት ወቅት ደረሰ፣ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ 58 ጎረቤቶቿና ዘመዶቿ እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዳበዛላት ሰሙ፣ ከእርሷም ጋር ደስ አላቸው፡፡ 59 ልጁን የሚገርዙበት ስምንተኛው ቀን በመጣ ጊዜ፣ በአባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊሰይሙት ፈልገው ነበር፡፡ 60 እናትዬዋ ግን መልስ ሰጠቻቸው፣ “አይሆንም፣ ስሙ ዮሐንስ ይሆናል” አለች፡፡ 61 እነርሱም ለእርሷ፣ “ከዘመዶችሽ መካከል በዚህ ስም የተጠራ የለም” አሏት፡፡ 62 በምን ስም እንዲጠራ እንደሚፈልግ አባቱን በምልክት ጠየቁት፡፡ 63 አባቱም ሰሌዳ እንዲያቀርቡለት ጠየቀና፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፡፡ በዚህም ሁሉም ተደነቁ፡ 64 ወዲያውኑም አንደበቱ ተከፈተ፣ ምላሱም ተፈትቶ ተናገረ፣ እግዚአብሔርንም አመሰገነ፡፡ 65 በዙሪያቸውም በሚኖሩት ሰዎች ዘንድ ፍርሃት መጣባቸው፣ የእነዚህም ነገሮች ዜና በኮረብታማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተሠራጨ፡፡ 66 ዜናውን የሰሙትም ሁሉ፣ የእግዚአብሔር እጅ ከእርሱ ጋር ነበርና “እንግዲህ ይህ ልጅ ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ጠበቁት፡፡ 67 አባቱም ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ 68 “የእስራኤል አምላክ፣ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፣ የመቤዠት ሥራ በመሥራት ሕዝቡን ረድቶታልና፡፡ 69 ከባሪያው ከዳዊት ዝርያዎች መካከል ለባሪያው ለዳዊት ቤት የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፡፡ 70 ይህም በጥንት ዘመን በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ እንደ ተናገረው ነው፡፡ 71 ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ ያድነናል፡፡ 72 ይህንን የሚያደርገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየትና ቅዱስ ኪዳኑን፣ 73 ማለትም ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማስታወስ ነው፡፡ 74 መሐላውን የማለውም እኛ ከጠላቶቻችን ድነን በዘመኖቻችን ሁሉ በእርሱ ፊት በመሆን ያለ ፍርሃት፣ 75 በቅድስናና በጽድቅ እርሱን እንድናገለግለው ነው፡፡ 76 አዎን፣ አንተም ሕፃን የእርሱን መንገድን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ስለምትሄድና ሕዝብንም ለመምጣቱ ስለምታሰናዳ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፡፡ 77 ለኃጢአቶቻቸው ይቅርታ የሚያገኙትን የድነት ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ 78 ይህም ከእግዚአብሔር አምላካችን መልካም ምሕረት የተነሣ ከእርሱ የተነሣ የፀሐይ ብርሃን በእኛ ላይ እንዲያርፍብንና 79 በጨለማና በሞት ጥላ ላሉት እናበራላቸው ዘንድ ነው፡፡ ይህንንም እግሮቻችንን በሰላም መንገድ ይመራው ዘንድ ያደርገዋል፡፡” 80 ልጁም አደገ፣ በመንፈሱም ጠነከረ፣ ለእስራኤልም እስኪገለጥ ድረስ በምድረ በዳ ኖረ፡፡