1 ያህዌ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣ 2 “ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ በሏቸው፣ ‘በምድር ላይ ከሚገኙ እንስሳት ሁሉ የምትመገቧቸው ህያዋን ነገሮች እነዚህ ናቸው፡፡ 3 የተሰነጠቀ ሰኮና ያላቸውንና የሚያመሰኩትን ትመገባላችሁ፡፡ 4 ሆኖም፣ የሚያመሰኩ ቢሆኑም ነገር ግን የተሰነጠቀ ሰኮና የሌላቸውን እንደ ግመል ያሉትን አትብሉ፤ምክንያቱም ያመሰኳሉ ነገር ግን ሰኮናው አልተሰነጠቀም፡፡ ስለዚህ ግመል ለእናንተ ንጹህ አይደለም፡፡ 5 እንዲሁም ሽኮኮ ያመሰኳል ነገር ግን የተሰነጠቀ ሰኮና የለውም፣ ይህም ለእናንተ ንጹህ አይደለም፡፡ 6 ጥንቸል ቢያመሰኳም የተሰነጠቀ ሰኮና ስለሌለው ለእናንተ ንጹህ አይደለም፡፡ 7 አሳማ የተሰነጠቀ ሰኮና ቢኖረውም፣ አያመሰኳም ስለዚህ ለእናንተ ንጹህ አይደለም፡፡ 8 የእነዚህን ስጋ ፈጽሞ አትብሉ፣ ጥንባቸውንም አትንኩ፡፡ እነርሱ ለእናንተ ንጹህ አይደሉም፡፡ 9 በውቂያኖስም ሆነ በባህር በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ እንስሳት የምትበሏቸው ክንፍና ቅርፊት ያላቸው ናቸው፡፡ 10 ነገር ግን በውቂያኖስ ወይም በባህር የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ህያዋን ፍጥረታት ሁሉ፣በውሃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ጨምሮ እንዲሁም በውሃ ውስጥ ያሉት እንዲህ ያሉ ህያዋን ፍጥረታት በሙሉ በእናንተ ዘንድ ጸያፍ ናቸው፡፡ 11 ጸያፍ ሊሆኑ ስለሚገባቸውም፣ ስጋቸውን ልትበሉ አይገባም፣ እንደዚሁም በድናቸውም ጸያፍ ነው፡፡ 12 በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ቅርፊት የሌላቸው እንስሳት ሁሉ፣በእናንተ ዘንድ ጸያፍ ናቸው፡፡ 13 ልትጸየፏቸው የሚገቡና የማትበሏቸው ወፎች እነዚህ ናቸው፤ ንስር፣ ጥንብ አንሳ፣ 14 ጭላት፣ ማንኛውም አይነት የሎስ 15 ማንኛውም አይነት ቁራ፣ 16 የተለያ አይነት ጉጉት፣ የባህር ወፍ እና ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፡፡ 17 ትናንሽና ትላልቅ ጉጉቶችን ትጸየፋላችሁ፣ርኩምና ጋጋኖ፣ 18 የተለያዩ ጉጉቶች፣ ይብራ፣ 19 ሽመላ፣ ማናቸውም ዐይነት የውሃ ወፍ፣ ሳቢሳ፣ ጅንጁላቲ ወፍና የለሊት ወፍ፡፡ 20 በእግራቸው የሚራዱ ክንፍ ያላቸው በራሪ ነፍሳት በሙሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ናቸው፡፡ 21 ሆኖም ግን ከእግራቸው በላይ በምድር ላይ የሚፈናጠሩበት አንጓ ያላቸውን ማናቸውንም የሚበሩ ነፍሳት መብላት ትችላላችሁ፡፡ 22 እንደዚሁም ደግሞ ማናቸውንም ዐይነት አንበጣ፣ ትልቅ የአንበጣ ዝርያ፣ ፌንጣና ዝንቢት መብላት ትችላላችሁ፡፡ 23 ነገር ግን አራት እግር ያላቸው የሚበሩ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጠሉ ናቸው፡፡ 24 ከእነዚህ እንስሳት ውስጥ የአንዱን በድን ብትነኩ እስከ ማታ ድረስ የረደሳችሁ ናችሁ፡፡ 25 ከእነዚህ የአንዱን በድን ያነሳ ማንም ሰው ልብሱን ይጠብ፣ እስከ ማታ ድረስ እርኩስ ነው፡፡ 26 ማንኛውም ሙሉ ለሙሉ ያልተሰነጠቀ ሰኮና ያለው እንስሳ ወይም የማያመሰኳ እንስሳ በእናንተ ዘንድ ጸያፍ ነው፡፡ እነዚህን የነካ ሁሉ ይረክሳል፡፡ 27 በአራት እግሩ ከሚራመድ እንስሳ መሃል በመዳፋቸው የሚሄዱ ሁሉ በእናንተ ዘንድ እርሱስ ናቸው፡፡ እንደነዚህ ያሉትን በድናቸውን የነካ እስከ ማታ እርኩስ ነው፡፡ 28 እንደነዚህ ያሉትን በድናቸውን ያነሳ ልብሱን ይጠብ እስከ ማታ ድረስ እርኩስ ይሆናል፡፡ እነዚህ እንስሳት በእናንተ ዘንድ እርኩስ ናቸው፡፡ 29 በምድር ላይ ከሚሳቡ እንስሳት መሃል፣ በእናንተ ዘንድ እርኩስ የሆኑት እነዚህ ናቸው፡ አቁስጣ፣ አይጥ፣ ማናቸውም አይነት እንሽላሊት 30 ትንሽ የቤት ላይ እንሽላሊት እና እስስት 31 ከሚሳቡ እንስሳት በእናንተ ዘንድ እርኩስ የሆኑት እነዚህ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የሞቱትን አንዳቸውን የነካ ሰው እስከ ምሽት እርሱስ ይሆናል፡፡ 32 ከእነዚህ መሃል አንዱ ሞቶ በማናቸውም ከእንጨት፣ ከጨርቅ፣ ከቆዳ ወይም ከበርኖስ በተሰራ ነገር ላይ ቢወድቀቅ ያዕቃ እርኩስ ይሆናል፡፡ ዕቃው ምንም ይሁን ለምንም አይነት ተግባር ይዋል ውሃ ውስጥ ይነከር እስከ ምሽት ድረስ እርኩስ ነው፡፡ ከዚያ ንጹህ ይሆናል፡፡ 33 ንጹህ ያልሆነ እንስሳ የገባበት ወይም የነካው የሸክላ ማሰሮ እንዲሁም በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ እርኩስ ይሆናል፤ ያንን ማሰሮ ሰባብረው፡፡ 34 ማናቸውም ለመበላት የተፈቀደ ምግብ፣ ንጹህ ካልሆነ ማሰሮ ውሃ ቢገባበት እርኩስ ይሆኖል፡፡ እንዲህ ካለው ማሰሮ ማንኛውም ነገር ቢጠጣ ያረክሳል፡፡ 35 እርኩስ ከሆነ እንስሳ በድን ማናቸውም አካሉ የወደቀበት ምድጃም ሆነ የማብሰያ ሸክላ እንዲሁም ማንኛውም ነገር ይረክሳል፡፡ ይሰባበር፡፡ እርኩስ ነው፣ በእናንተም ዘንድ የተጠላ ይሁን፡፡ 36 የመጠጥ ውሃ የሚገኝበት ምንጭ ወይም የውሃ ጉድጓድ እንዲህ ያሉ እንስሳት ቢገኙበትም ንጹህ ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው በውሃው ውስጥ የሚገኘውን እርኩስ የሆነውን በድን ቢነካ እርኩስ ይሆናል፡፡ 37 ንጹህ ያልሆነ እንስሳ በድን በዘር ላይ ቢወድቅ፣ እነዚያ ዘሮች የረከሱ ይሆናሉ፡፡ 38 ነገር ግን በዘሮቹ ላይ ውሃ ቢፈስ ንጹህ ያልሆነው እንስሳ በድን ማንኛውም አካል የተክል ዘሩ ላይ ቢወድቅ ዘሩ በእናንተ ዘንድ እርኩስ ይሆናል፡፡ 39 ለመበላት ከተፈቀደው እንስሳ አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የነካው ሰው እስከ ምሽት እርኩስ ይሆናል፡፡ 40 ደግሞም እንዲህ ያለውን በድን ያነሳ ሰው ልብሱን ያጥባል፣ እስከ ምሽት ድረስ እርኩስ ይሆናል፡፡ 41 41ማንኛውም በምድር ላይ የሚሳብ እንስሳ ጸያፍ ነው፤ አይበላም፡፡ 42 42በሆዱ የሚሳብ እንስሳ ሁሉ፣ እና በአራቱም እግሮቹ የሚራመድ፣ወይም ማንኛውም ብዙ እግሮች ያሉት - በምድር የሚሳብ እንስሳን ሁሉ፣ አትብሉ፤ እነዚህ ጸያፍ ናቸው፡፡ 43 በደረቱ በሚሳብ ማናቸውም ህያው ፍጥረት ራሳችሁን አታርክሱ፤ እነዚህ እናንተን ያረክሳሉ፡፡ 44 እኔ አምላካችሁ ያህዌ ነኝ፡፡ በምድር በሚንቀሳቀስ በማናቸውም አይነት እንስሳ ራሳችሁን አታርክሱ፡፡ 45 እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ ያህዌ ነኝ፡፡ ስለዚህ እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱስ መሆን አለባችሁ፡፡ 46 ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በውሃ ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ማናቸውም ህያዋን ፍጥረታት፣ እንዲሁም በምድር ላይ ስለሚሳቡ ፍጥረታት ህጉ ይህ ነው፤ 47 ንጹህ ባልሆኑና ንጹህ በሆኑት መካከል ልዩነት ለመፍጠር፣ እና በሚበሉ ህያዋን ነገሮችና በማይበሉ ህያዋን ነገሮች መሃል ለመለየት ህጉ ይህ ነው፡፡’”