ምዕራፍ 1

1 በሰዎች ተሞልታ የነበረችው ከተማ አሁን ፈጽማ ብቻዋን ተቀምጣለች! ኃያል የነበረችው አገር እንደ መበለት ሆናለች! በሕዝቦች መካከል እንደ ልዕልት ነበረች፥ አሁን ግን በባርነት ውስጥ ወድቃለች! 2 በሌሊት ታለቅሳለች፥ታነባለችም፤እንባዎቿም ጉንጮቿን ከድነዋል። ከፍቅረኞቿ መካከል የሚያጽናናት የለም። ጓድኞቿ ሁሉ አሳልፈው ሰጧት። ጠላቶቿም ሆነዋል። 3 ከድህነቱና ከመከራዉ የተነሳ ይሁዳ ወደ ምርኮ ሄደች። በሕዝቦች መካከል ኖረች፥ ዕረፍትንም አላገኘችም። በጭንቀቷ ጊዜ አሳዳጆቿ ሁሉ በረቱባት። 4 ወደ ተቀጠሩት በዓላት የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ። ደጆቿ ሁሉ ባዶ ናችው። ካህናቶቿ ይቃትታሉ። ደናግሎቿ ሐዘንተኞች ናቸዉ፥እራስዋም በፍጹም ጭንቀት ውስጥ አለች። 5 ባላንጣዎቿ ጌቶቿ ሆኑ፥ጠላቶቿ በለጸጉ። ስለ ብዙ ኃጢአቷ እግዚአብሔር መከራን አመጣባት። ልጆቿ ለጠላቷ ተማርከው ወደ ግዞት ሄዱ። 6 የጽዮን ሴት ልጅ ውበቷ ተለያት። ልዑላኖቿ መሰማሪያ እንዳላገኙ አጋዘኖች ሆኑ፥ በአሳዳጆቻቸው ፊት በድካም ሄዱ። 7 በመከራዋና ቤት አልባ በሆነችባቸው ቀናት፥ ኢየሩሳሌም በቀደሙት ቀናት የነበሯትን የከበሩ ነገሮች ታስባለች፤ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ ማንም የረዳት አልነበረም። ጠላቶቿ ተመለከቷት፥ በጥፋቷም ሳቁ። 8 ኢየሩሳሌም ታላቅ ኃጢአት ሠርታለች፥ ስለዚህ እንደ አደፈ ነገር ተንቃለች። ዕርቃናዋን ከተመለከቱበት ጊዜ አንስቶ ያከበሯት ሁሉ ናቋት። ታጉተመትማለች፥ ዘወር ለማለትም ትሞክራላች። 9 ከቀሚሷ በታች አድፋለች። የወደፊቷን አላሰበችም። አወዳደቋ አስፈሪ ነበር። የሚያጽናት ማንም አልነበረም። « እግዚአብሔር ሆይ፥ መከራዬን ተመልከት፥ ጠላት እጅግ ታላቅ ሆኖአልና» እያለች ትጮኻለች!። 10 ጠላት በከበረ ነገሯ ሁሉ ላይ እጁን አደረገ። ወደ ጉባዔህ እንዳይገቡ አዝዘህ የነበረ ቢሆንም እንኳን፥ ሕዝቦች ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች። 11 ሕዝቦቿ ሁሉ ምግብ እየፈለጉ ይጮኻሉ። ሕይወታቸውን ለማቆየት የከበረ ኃብታቸውን ስለ ምግብ ይሰጣሉ። የማልጠቀም ሆኟለሁና፥ እግዚአብሔር ሆይ ተመልከት አስበኝም። 12 እናንተ መንገደኞች ሁሉ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን? እግዚአብሔር እኔን መቅጣት ከጀመረበት ከጽኑ ቁጣው ቀን አንስቶ፥ የደረሰብኝን ሐዘን የሚመስል የማንም የሌላ ሰው ሐዘን ካለ ተመልከቱ፥ እዩም። 13 ወደ ዉስጥ ወደ አጥንቶቼ ከላይ እሳት ላከ፥ አሸነፋቸዉም። ለእግሮቼ መረብን ዘረጋ ወደ ኋላም መለሰኝ። ያለማቋረጥ ባዶና ደካማ አደረገኝ። 14 የመተላለፌ ቀንበር በእጆቹ በአንድ ላይ ታስረዋል። በአንድ ላይ ተገምደዋል፥በአንገቴም ላይ ተደርገዋል። ብርታቴን ከንቱ አደረገው። ጌታ በእጃቸው አሳልፎ ሰጠኝ፥ መቆምም አልችልም። 15 ጌታ፥የሚመክቱልኝን ኃያላን ወንዶች ሁሉ ወዲያ ጣላቸው። ጽኑዓን ወንዶቼን ለማድቀቅ ጉባዔን በላዬ ጠራብኝ። ጌታ ድንግሊቱን የይሁዳ ልጅ በወይን መጥመቂያ እንዳለ ወይን ረገጣት። 16 ስለ እነዚህ ነገሮች አለቅሳልሁ። ሕይወቴን የሚያድሳት አጽናኙ ከእኔ ርቋልና ከዓይኖቼ ውኃ ይፈሳል፥ ከዓይኖቼ። 17 ጽዮን እጆቿን እጅግ ዘረጋች፥ የሚያጽናናት ማንም የለም። እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉ ጠላቶቹ እንዲሆኑ አዘዘ። ኢየሩሳሌም በእነርሱ ዘንድ እንደ ርኩስ ነገር ተቆጠረች። 18 በትዕዛዙ ላይ ዐመጽ አድርጌእለሁና እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፥ ሐዘኔንም ተመልከቱ። ደናግሎቼና ኃያላን ወንዶቼ ተማርከዉ ሄደዋል። 19 ፍቅረኞቼን ጠራኋቸው፥ ነገር ግን ከዳተኞች ሆኑብኝ። ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ ሕይወታችውን ለማኖር ምግብ እየፈለጉ በከተማ ውስጥ ሞቱ። 20 እግዚአብሔር ሆይ ተጨንቄአለሁና ውስጤም ተንጦአልና ተመልከት። እጅግ ዓመጽ አድርጌአለሁና ልቤ በውስጤ ታውኮአል። በመንገዶች ላይ ሰይፍ ልጆቻችንን ይነጥቃል፥በቤትም እንደ ሙታን መንደር ነው። 21 ሲቃዬን ስማ። የሚያጽናናኝ ማንም የለም። ጠላቶቼ ሁሉ ስለ መከራዬ ሰምተዋል። አንተ ስለ አደረግከው ደስ አላቸው። እነርሱም እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ ያወጅክባቸውን ቀን አምጣ። 22 ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይታይ። መቃተቴ ብዙ ነውና፥ ልቤም ደክሞአልና፤ስለ መተላለፌ ሁሉ እንዳሰቃየኽኝ አሰቃያቸው።