ምዕራፍ 1

1 በአንድ ወቅት ኢየሩሳሌም፣ ሕዝብ ሞልቶባት ነበር፣ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ የተተወች ሆናለች፡፡ በአንድ ወቅት ኃያል አገር ነበረች፣ አሁን ግን ባል እንደ ሞተባት ሴት ብቻዋን ቀርታለች፡፡ በአንድ ወቅት በዓለም ያሉ ሁሉ እንደ ልዕልት ያከብሯት ነበር፣ አሁን ግን እንደ ባሪያ ሆናለች፡፡ 2 በከተማይቱ ያለን እኛ ሌሊቱን በሙሉ መራራ ልቅሶ እናለቅሳለን፣ እንባዎቻችን በጉንጮቻችን ላይ እያወረድን እንዲረዳን በእግዚአብሔር አልታመንንም፣ እምነት የጣልንባቸው ወገኖችም ሊረድን አልቻሉም፤ ከእነዚያ ሰዎች መካከል የሚያጽናናን አንድም የለም ወዳጆቻችን የነበሩ እነዚያ ወገኖች ሁሉ ከድተውናል፤ አሁን እነርሱ ሁሉ ጠላቶቻችን ሆነዋል፡፡ 3 ሕዝብ ደኽይተዋል ብዙ ሥቃይም ደርሶባቸዋል፡፡ ከሕዝባችን ብዙዎቹ ከአገራችን እንዲወጡ ተገደዱ፡፡ አሁን እኛ በሌላ አገር እየኖን ነው ሰላምም የለንም፡፡ ጠላቶቻችን የማረኩን እኛ የይሁዳ ሕዝብ ራሳችን መከላከል ባልቻልን ጊዜ ነበር፡፡ 4 ከእንግዲህ የተቀደሱትን በዓላት ለማክበር ማንም ስለማይመጣ፣ ወደ ጽዮን ተራራ የሚወስዱት መንገዶች ባዶ ናቸው፡፡ ከእንግዲህ ለመነጋገር ከከተማይቱ በሮች በታች ተቀምጠው የሚነጋገሩ ሽማግሌዎች ወይም መሪዎች አይኖሩም፣ የኢየሩሳሌም ካህናትም በሐዘን ይቃትታሉ፡፡ ብዙ ሥቃይ እየደረሰባቸው በመሆኑ በኢየሩሳሌም የቀሩ ቈነጃጅት ያለቅሳሉ፡፡ 5 የከተማችን ገዢዎች ሆነዋል፣ ተሳክቶላቸዋልም፡፡ ስላደረግናቸው ኃጢአቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር እኛን የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ቀጥቶናል፡፡ ጠላቶቻችን ልጆቻችንን ሁሉ ወስደው ወደ ሌሎች አገሮች እንዲሰደዱ አድርገዋቸዋል፡፡ 6 ኢየሩሳሌም የምታምር ከተማ ነበረች፣ አሁን ግን ውበቷ የለም፡፡ የከተማችን መሪዎች ሣር አጥተው እንደ ተራቡ አጋዘኖች ናቸው፡፡ በጣም ደካሞች በመሆናቸው ከጠላቶቻችን ሸሽተው ማምለጥ አይችሉም፡፡ 7 እኛ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሐዘንተኞች ነን ከእንግዲህም መኖሪያ ቤቶች የሉንም፤ አንድ ጊዜ ከተማችንን ሞልተው የነበሩትን የከበሩ ነገሮች ሁሉ እናስባለን፡፡ አሁን ግን ጠላቶቻችን ከተማይቱን ይዘዋታል፣ የሚረዳንም ማንም የለም፡፡ ጠላቶቻችን እየተሳለቁ ከተማችንን አፈረሷት፡፡ 8 የኢየሩሳሌም ሕዝብ በጣም ብዙ ኃጢአት ሠርተናል፤ ከተማችን በሴት ጭኖች መካከል እንዳለ የመርገም ጨርቅ ሆናለች ቀድሞ ያከብሯት የነበሩ ሁሉ አሁን ንቀዋታል፤ የሴቷን ልብስ ገፈው ራቊቷን ባስቀሯት ሴት እንደሚሳለቁ ሰዎች ናቸው፡፡ አሁን እኛ በከተማይቱ እንቃትታለን፤ ልብስ እንደሌላትና በእጆቿ ሰውነቷን ለመሸፈን እንደምትሞክር ሴት ነን፡፡ 9 በጣም ብዙ ኃጢአት ከተማችን የቆሸሸች ያህል ናት እግዚአብሔር እንዴት እንደሚቀጣን አላሰብንም፡፡ እንዴት ያለ ሥቃይ እንደሚደርስብንም አልተመትንም የሚያጽናናን ማንም የለም፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሆይ፣ ጠላቶቻችን ስላሸነፉን እንዴት እየተሠቃየን እንዳለን ተመልከት!›› በማለት ሁላችንም ወደ እግዚአብሔር እንጮኻለን፡፡ 10 ጠላቶቻችን የከበሩ ነገሮቻችን ሁሉ፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶቻችንንም ሁሉ ዘረፉ፡፡ አምላክ ሆይ፣ ሕዝብህ አንተን ወደሚያመልኩበት፣ ባዕድ መግባት የለበትም ወዳልኸው ወደ ተቀደሰው መቅደሳችን አንተን የማያመልኩ ሕዝብ እየገቡ ናቸው፡፡ 11 ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግብ እየፈለጉ ሳሉ የሲቃ ጩኸት ይጮኻሉ፡፡ ብርታታቸው እንዲመለስላቸው የሚበሉትን ምግብ ለማግኘት እጅግ በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡ አምላክ ሆይ፣ እኔን ተመልከተኝ፣ ማንም ለሕይወቴ ዋጋ አይሰጣትም፡፡ 12 በኩል የምታልፉ እናንተ ሰዎች፣ በእኔ ላይ ስላደረሰው ነገር በጭራሽ ግድ ያላችሁ አትመስሉም፡፡ በእኔ ላይ እንደደረሰው ያለ ሥቃይ የደረሰባቸው ሌሎች ሰዎች እንደሌሉ እስቲ ዘወር ብላችሁ ተመልከቱ እዩም፡፡ እግዚአብሔር በእኛ በሕዝቡ ላይ በተቈጣበት ቀን እኔን ስለ ቀጣኝ እንድሠቃይ አድርጐኛል፡፡ 13 የሚቃጠል፤ እሳት ከሰማይ የላከ ያህል ተሰማኝ ተራምጄ ወደ ቤታችን እንዳልመለስ እግሮቼን ለመያዝ ወጥመድ አድርጐ የከለከለኝ ያህል ነበር እሱ እኔን ትቶኛል፤ ቀኑን ሁሉ ደካማና ብቸኛ ነኝ፡፡ 14 ኃጢአቶች የምሸከማቸው ከባድ ሸክሞች አድርጐ በአንገቴ ዙሪያ ያሰራቸው ያህል ነበር በቀድሞ ጊዜ እኛ ብርቱዎች ነበርን፣ ነገር ግን እሱ እኔን አደከመኝ፡፡ ጠላቶቼ እንዲማርኩኝ ፈቀደላቸው፣ እኔም እነርሱን ለመቋቋም ምንም ማድረግ አልቻልሁም፡፡ 15 ደኅንነቴን የጠበቁትን ኃያላን ወታደሮቼን ተመለከተ ብርቱዎች የሆኑትን ወጣት ወታደሮቼን አሸንፎ መጥቶ የሚያደቀኝን ታላቅ ሠራዊ ሰበሰበ፡፡ ሰዎች ወይን ለመጭመቅ በጉድጓድ የወይን ዘለላ እንደሚረግጡ፣ እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ረገጣቸው፡፡ 16 በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ምክንያት አለቅሳለሁ፡፡ ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፡፡ የሚያጽናናኝ ማንም የለም፡፡ የሚያጽናናኝ ከእኔ ርቆአል፡፡ ጠላት ሁላችንንም ማርኮ ስለወሰደን ልጆቼ ተስፋ የላቸውም፡፡ 17 (በኢየሩሳሌም ከተማ) የኖሩ ማንም የሚያጽናናቸው የለም፡፡ በጐረቤት አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች የአባታችን የያዕቆብ ዝርያዎች እስራኤላውያን ተብለው የሚጠሩት ጠላቶች እንዲሆኑ እግዚአብሔር አዟል፡፡ ኢየሩሳሌም ለእነርሱ አስጸያፊ ሆናለች፡፡ 18 ነገር ግን አድርገው ብሎ የነገረኝን ለመታዘዝ አሻፈረኝ በማለቴ፣ እግዚአብሔር በእኔ ላይ ያደረገው ነገር ትክክለኛ ነው፡፡ በሁሉም ቦታ ያላችሁ እናንተ ሕዝቦች ሆይ፣ አድምጡኝ! በእጅጉ እየተሠቃየሁ መሆኔን ተመልከቱ እዩም፡፡ ሴቶች ልጆቼና ጀግኖች ወንዶች ልጆቼ ወደ ሩቅ አገሮች ተማርከው ተወስደዋል፡፡ 19 ይረዱናል ብለን የተማመንባቸውን ተባባሪዎቻችን ለመንሁ፣ እነርሱ ሁሉ ግን አሻፈረን አሉ፣ ውሸት ተናገሩ ቃላቸውንም አልጠበቁም፡፡ ካህናቴና መሪዎቼ የሚበሉትን ምግብ በመፈለግ ላይ እያሉ በከተማይቱ ቅጥር ውስጥ ሞቱ፡፡ 20 እግዚአብሔር ሆይ፣ በጣም እየተሰቃየሁ መሆኔን ተመልከት! በውስጤ ትልቅ ጭንቀት አለ፡፡ በአንተ ላይ ስላመፀሁና እጅግ ስላሳዘንሁህ፣ ልቤ ዐዝኖአል! በመንገዶች ላይ ጠላቶቻችን በሰይፎቻቸው ሰዎችን ይገድላሉ፤ ይህም ቤቶቻችንን የሙታን መጣያ ስፍራዎች አድርጓቸዋል፡፡ 21 ሰምተዋል! ነገር ግን ማንም ሊያጽናናኝ አልመጣም፡፡ ጠላቶቻችን ሁሉ በእኔ ላይ የደረሰውን ያው ቃሉ፤ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያደረገውን በመስማታቸው ሁላቸውም ደስተኞች ነበሩ እኛ እንደ ተሠቃየን ጠላቶቻችንም እንዲሠቃዩ የገባኸውን ቃል ፈጥነህ አድርግ! 22 እግዚአብሔር ሆይ፣ ሁላቸውንም ልታያቸው እንድትችል እነዚያ ክፉ ድርጊቶች ወደ አንተ እንዲቀርቡ አድርግ! ስለ ኃጢአቶቼ ሁሉ እኔን እንደ ቀጣኸኝ እነርሱንም ቅጣቸው! እሰቃያለሁ ደግሞም በጣም ብዙ እቃትታለሁ፣ በውስጤም ዝለት ይሰማኛል፡፡