ምዕራፍ 1
1
የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ፥ የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤ ለተጠሩት፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት፤
2
ምሕረት ለእናንተ ይሁን፤ ሰላምና ፍቅርም ይብዛላችሁ።
3
ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ ጥረት እያደረግሁ ሳለ፥ ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለተሰጠው እምነት ጸንታችሁ ትጋደሉ ዘንድ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።
4
ለፍርድ እንደሚዳረጉ ከብዙ ዘመን በፊት የተጻፈባቸው አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና። እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌላቸው፥ የእግዚአብሔርን ጸጋ በሴሰኝነት የሚለውጡ፥ እርሱ ብቻ ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።
5
ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ሁሉን የምታውቁት ቢሆንም ጌታ አንድ ጊዜ ሕዝቡን ከግብጽ አውጥቶ እንደ አዳናቸው በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋቸው ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።
6
እንዲሁም የነበራቸውን የሥልጣን ደረጃ ባለመጠበቅ ተገቢ የመኖሪያ ስፍራቸውን የተውትን መላእክት እግዚአብሔር እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓል።
7
እንዲሁም ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩት ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ ራሳቸውን ለሴሰኝነትና ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ ለሆነ ግብረ ሥጋ ግንኙነት አሳልፈው ሰጡ፤ እነርሱም በዘላለም እሳት ተጥለው ለሚሰቃዩት ምሳሌ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
8
በዚህ ሁኔታ እነዚህ ደግሞ በሚያልሙት ሕልማቸው የራሳቸውን ሥጋ ያረክሳሉ፤ሥልጣንን ይቃወማሉ፤በሰማይ ክብር ያላቸውንም ይሳደባሉ።
9
የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳ ዲያብሎስን በመቃወም ስለ ሙሴ ሥጋ በተከራከረው ጊዜ «ጌታ ይገሥጽህ» አለው እንጂ በእርሱ ላይ ሊፈርድ ወይም አንዳች የስድብ ቃል ሊናገር አልደፈረም።
10
እነዚህ ሰዎች ግን የማያውቋቸውን ነገሮች ሁሉ ይሳደባሉ። እነርሱም አእምሮ የሌላቸው እንስሳት እንደሚያደርጉት በደመ ነፍስ በሚያውቋቸው ነገሮች ይጠፋሉ።
11
ወዮላቸው፤ በቃየን መንገድ ሄደዋልና፤ለገንዘብ ሲሉ በበለዓም ስህተት ውስጥ ወድቀዋልና፤በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋልና።
12
እነዚህ በፍቅር ግብዣችሁ ላይ አብረዋችሁ ሲጋበዙ ችግር የሚፈጥሩባችሁ ድብቅ እንቅፋቶች ናቸው፤ ደግሞም ያለ ሃፍረት ራሳቸውን ብቻ የሚመግቡ እረኞች ናቸው። እነርሱም በነፋስ የሚነዱ ውሃ አልባ ደመናዎች ናቸው፤ በመከር ወራት ፍሬ የማይገኝባቸው፥ ከሥራቸው የተነቀሉና ሁለት ጊዜ የሞቱ ዛፎች ናቸው።
13
የራሳቸውን የነውር አረፋ የሚደፍቁ የተቆጣ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማም ለዘላለም የተጠበቀላቸው ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።
14
ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሯል፤ «እነሆ፤ ጌታ ከብዙ ሺህ ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል።
15
የሚመጣውም በሰው ሁሉ ላይ ለመፍረድ እንዲሁም ዐመፀኞችንና ኀጢአተኞችን ክፋት በተሞላበት ሁኔታ በፈጸሙት የዐመፅ ሥራቸውና በእግዚአብሔር ላይ በተናገሩት የስድብ ቃል ለመውቀስ ነው።»
16
እነዚህ የሚያጉረመርሙ፥ ሌላውን የሚከሱ፥ የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ፥ ጉራ የሚነዙና ጥቅም ለማግኘትም ሰዎችን የሚክቡ ናቸው።
17
እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን ቃል አስታውሱ
18
ለእናንተም ሲናገሩ፥«በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ» ብለዋል።
19
እነዚህ በሰዎች መካከል መለያየትን የሚፈጥሩ፥የሥጋን ምኞት የሚከተሉና መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ናቸው።
20
እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ።
21
በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ፤የዘላለም ሕይወትም ታገኙ ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ፈልጉ።
22
ለሚጠራጠሩ ሰዎች ርኅራኄ አድርጉላቸው፤
23
ከእሳት ነጥቃችሁ በማውጣት አንዳንዶችን አድኑ፤ ለሌሎች ድግሞ በእርኩስ ሥጋ የተበከለውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ምህረት አሳዩአቸው።
24
እንግዲህ ከመውደቅ ሊጠብቃችሁ፥ ነቀፋ ሳይኖርባችሁ በታላቅ ደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው
25
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት አዳኛችን ለሆነው ብቸኛ አምላክ ከዘመናት ሁሉ በፊት፥ አሁንና እስከ ዘላለም ድረስ ክብር፥ ግርማ፥ ኀይልና ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።