ምዕራፍ 1

1 በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ 2 ይህም ቃል ከመጀመሪያው ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፡፡ 3 ሁሉም ነገር የተሠራው በእርሱ አማካይነት ነው፤ ከተሠሩት ነገሮች ሁሉ ያለ እርሱ የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም፡፡ 4 በእርሱ ሕይወት ነበረ፤ያም ሕይወት የሰው ሁሉ ብርሃን ነበር፡፡ 5 ብርሃኑ በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም ሊያጠፋው አልቻለም፡፡ 6 ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፡፡ 7 ሁሉም በእርሱ እንዲያምኑ እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ። 8 ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ ዮሐንስ ራሱ ብርሃን አልነበረም፡፡ 10 እርሱ በዓለም ውስጥ ነበር፤ ዓለሙም የተሠራው በእርሱ ነው፤ ዓለም ግን አላወቀውም፤ 11 የራሱ ወደ ሆኑት መጣ፤ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም፡፡ 12 ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው፡፡ 13 እነርሱም ከደምና ከሥጋ ወይም ከሰው ፈቃድ አልተወለዱም፤ ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፡፡ 14 ቃል ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም ዐደረ፤ እኛም ጸጋና እውነት የተሞላውን ከአብ ዘንድ ያለውን የአንድያ ልጁን ክብር አየን፡፡ 15 ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ፣ «ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ ይበልጣል፤ 'ከእኔ በፊት ነበርና' ያልኋችሁ ይህ ነው» ይል ነበር፡፡ 16 ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን፤ 17 ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ በኩል መጣ፡፡ 18 በየትኛውም ጊዜ እግዚአብሔርን ያየው አንድም ሰው የለም፤ ነገር ግን በአባቱ ዕቅፍ ያለውና እርሱ ራሱ እግዚአብሔር የሆነው አንድያ ልጁ እርሱ እግዚአብሔርን እንዲታወቅ አደረገው፡፡ 19 አይሁድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ልከው፣ «አንተ ማን ነህ?» ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው፡፡ 20 እርሱ በግልጽ ተናገረ አልካደምም፤ ነገር ግን፣ «እኔ ክርስቶስ አይደለሁም» ብሎ መለሰላቸው። 21 ስለዚህ እነርሱም፣ «ታዲያ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?» ብለው ጠየቁት፤ እርሱ፣ «አይደለሁም» አላቸው። እነርሱ፣ «ነቢዩ ነህን?» አሉት፤ እርሱ፣ «አይደለሁም» አለ፡፡ 22 ከዚያም እነርሱ፣ «ለላኩን መልስ መስጠት እንድንችል፣ አንተ ማን ነህ? ስለ ራስህስ ምን ትላለህ?» አሉት፡፡ 23 እርሱ፣ «ልክ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው፡- 'የጌታን መንገድ አስተካክሉ' እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ» አላቸው፡፡ 24 ከፈሪሳውያን የተላኩ ሰዎችም ነበሩ። 25 እነርሱ፣ «ክርስቶስ፣ ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንህ፣ ታዲያ ለምን ታጠምቃለህ?» ብለው ጠየቁት፡፡ 26 ዮሐንስ፣ «እኔ በውሃ አጠምቃለሁ፤ ይሁን እንጂ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሟል፤ 27 ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ነኝ» በማለት መለሰላቸው፤ 28 ይህ ሁሉ የሆንው ዮሐንስ ሲያጠምቅ በነበረበት በዮርዳኖስ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ነበር፡፡ 29 በማግስቱ ዮሐንስ ኢየሱስ ወደ እርሱ ሲመጣ ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ «እነሆ፣ የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ይኸውና! 30 'ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይበልጣል' ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ እርሱ ነው፡፡ 31 እኔ አላወቅሁትም ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ እኔ በውሃ እያጠመቅሁ መጣሁ፡፡» 32 ዮሐንስ እንዲህ ሲል መሰከረ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፡፡ 33 እኔ አላወቅሁትም ነበር፤ ነገር ግን በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝ እርሱ፣ 'መንፈስ ሲወርድበትና ሲያርፍበት የምታየው፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው እርሱ ነው' አለኝ፡፡ 34 እኔ ይህን አይቻለሁ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነም መስክሬአለሁ፡፡» 35 ደግሞም በማግስቱ፣ ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆሞ ሳለ፣ 36 ኢየሱስን በአጠገባቸው ሲያልፍ አዩት፤ ዮሐንስም፣ «እነሆ፣ የእግዚአብሔር በግ» አለ፡፡ 37 ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ዮሐንስ ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት፤ 38 ከዚያም ኢየሱስ መለስ ብሎ ሲከተሉት አየና፣ «ምን ትፈልጋላችሁ?» አላቸው:: እነርሱ፣ «ረቢ የት ነው የምትኖረው?» አሉት። ረቢ ማለት 'መምህር' ማለት ነው። 39 እርሱ፣ «ኑና እዩ» አላቸው፡፡ ከዚያም እነርሱ መጥተው የሚኖርበትን አዩ፤ በዚያም ቀን ዐብረውት ዋሉ፤ ሰዓቱም ዐሥረኛው ሰዓት ያህል ሆኖ ነበርና:: 40 ዮሐንስ ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ፡፡ 41 እርሱ በመጀመሪያ የራሱን ወንድም ጴጥሮስን አገኘውና፣ «መሲሑን አግኝተነዋል» አለው። መሲሕ 'ክርስቶስ ማለት ነው'፡፡ 42 ወደ ኢየሱስም አመጣው፡፡ ኢየሱስ ጴጥሮስን ተመለከተውና፣ «አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ ትባላለህ» አለው። ኬፋ 'ጴጥሮስ ማለት ነው'፡፡ 43 በማግስቱ፣ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ በፈለገ ጊዜ፣ ፊልጶስን አግኝቶ፣ «ተከተለኝ» አለው፡፡ 44 ፊልጶስም ጴጥሮስና እንድርያስ ከሚኖሩበት ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበር፡፡ 45 ፊልጶስ ናትናኤልን አገኘውና፣ «ሙሴ በሕግ፣ ነቢያትም በትንቢት የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስ አግኝተነዋል» አለው፡፡ 46 ናትናኤል፣ «ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን?» አለው፡፡ ፊልጶስም መጥተህ እይ አለው፡፡ 47 ኢየሱስ፣ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፣ «እነሆ፣ ተንኰል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ!» አለ። 48 ናትናኤል፣ «እንዴት ታውቀኛለህ?» አለው፡፡ኢየሱስም፣ «ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አየሁህ» ብሎ መለሰለት፡፡ 49 ናትናኤል፣ «አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ!» ብሎ መለሰለት፡፡ 50 ኢየሱስ፣ «ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ገና ከዚህ የሚበልጡ ነገሮችን ታያለህ» ብሎ መለሰለት፡፡ 51 ኢየሱስ፣ «እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማያት ሲከፈቱ መላእክትም በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ» አለ፡፡