1 ይህ የኬልቅያስ ልጅ የሆነው የኤርምያስ ቃል ነው፤ እርሱ በብንያም ምድር ከነበሩት ካህናት አንደኛው ነበር። 2 የአሞጽ ልጅ በሆነው በይሁዳ ንጉሥ ዐሥራ ሦስተኛ ዓመት አገዛዝ ዘመን ላይ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። 3 ቃሉ የመጣው በይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ በሆነው ኢዮአቄም ዘመን፣ የኢዮስያስ ልጅ በሆነው የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ የዐሥራ አንደኛው አመት አገዛዝ አምስተኛ ወር ድረስ፣ የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ምርኮኛ ሆነው ሲወሰዱ ነበር። 4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፣ 5 "በማኅፀን ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብ ነቢይ አድርጌሃለሁ።" 6 እኔም፣ "ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ ገና ብላቴና በመሆኔ እንዴት እንደምናገር አላውቅም" አልሁ። 7 ነገር ግን እግዚአብሔር "'ገና ብላቴና ነኝ' አትበል። ወደምልክህ ሁሉ ልትሄድ ይገባል፣ የማዝዝህንም ሁሉ ልትናገር ይገባል! 8 ላድንህ ከአንተ ጋር ስለሆንኩ አትፍራ - ይህ የእግዚአብሔር ንግግር ነው።" አለኝ። 9 እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፣ እንዲህም አለኝ "ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ 10 ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾሜሃለሁ" አለኝ። 11 የእግዚአብሔር ቃል "ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ?" እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም "የለውዝ በትር አያለሁ" አልሁት። 12 እግዚአብሔርም "መልካም አይተሃል፣ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና" አለኝ። 13 የእግዚአብሔር ቃል ለሁለተኛ ጊዜ "ምን ታያለህ?" እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም "ፊቱ ከሰሜን አቅጣጫ የሆነ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ" አልሁ። 14 እግዚአብሔርም "በዚህች ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ከሰሜን አቅጣጫ ክፉ ነገር ይገለጣል" አለኝ። 15 በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁና ይላል እግዚአብሔር። እነርሱም ይመጣሉ፣ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም መግቢያ በራፍ ላይ፣ በዙሪያዋ ባሉት በአጥሮቿ ሁሉ ላይ፣ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያኖራሉ። 16 እኔን ስለተዉበት ክፋታቸው ሁሉ፣ ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ፣ በገዛ እጃቸው ለሠሯቸውም ስለሰገዱላቸው፣ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 17 አንተ ራስህን አዘጋጅ! ተነሥና ያዘዝሁህን ሁሉ ንገራቸው። በእነርሱ ፊት አትፍራ፣ አሊያ እኔ በእነርሱ ፊት አስፈራሃለሁ! 18 ተመልከት! ዛሬ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት -በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገ ከተማ እንደ ብረትም ዓምድ እንደ ናስም ቅጥር አድርጌሃለሁ። 19 ይዋጉሃል፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም" ይላል እግዚአብሔር።