ምዕራፍ 1
1
በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር እስረኛና አገልጋይ የሆነ ያዕቆብ በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑና በመላው ዓለም ለተበተኑት ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡
2
ወንድሞቼ ሆይ፣ በልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ ማለፋችሁን እጅግ ደስ እንደሚያሰኝ ነገር ቊጠሩት፡፡
3
በፈተና ውስጥ ሳላችሁ በእግዚአብሔር ስታምኑ ይበልጥ ሌሎች ፈተናዎችን በትዕግሥት ለማሳለፍ የሚረዱዋችሁ መሆኑን ትረዳላችሁ፡፡
4
ክርስቶስን በሁሉም መንገድ ትከተሉ ዘንድ እስከ መጨረሻው በፈተና ጽኑ፤ ያንጊዜ መልካም ማድረግ አይከብዳችሁም፡፡
5
ከእናንተ አንዱ ምን ማድረግ እንዳለበት ማወቅ ከፈለገ፣ በሚጠይቀው ላይ ሳይቈጣ በልግሥና የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይጠይቅ፡፡
6
እግዚአብሔርን ስትለምኑ፣ የምትጠይቁትን እንደሚሰጣችሁ እመኑ፤ መልስ እንደሚሰጣችሁና ሁልጊዜም እንደሚረዳችሁ አትጠራጠሩ፤ የሚጠራጠሩ ሰዎች እግዚአብሔርን ሊከተሉት አይችሉም፤ መጠራጠር ልክ ተመልሶ እንደሚመጣ፣ ደግሞም በዚያው አቅጣጫ መጓዝን እንደማይቀጥል የባሕር ማዕበል ያለ ነገር ነው፡፡
7
በእርግጥ የሚጠራጠሩ ሰዎች የሚጠይቁትን ነገር ለመፈጸም እግዚአብሔር አንድ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል አያምኑም፡፡
8
እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመከተል ወይም ላለመከተል ያልወሰኑ ናቸው፤ እነዚህም የሚናገሩትን ነገር የማያደርጉ ሰዎች ናቸው፡፡
9
ድሀ የሆኑ አማኞች እግዚአብሔር ስላከበራቸው ደስ ሊሰኙ ይገባል፡፡
10
ባለጠጋ የሆኑ አማኞችም እግዚአብሔር ትሑታን ስላደረጋቸው ደስ ሊሰኙ ይገባል፤ ልክ የበረሃ አበቦች እንደሚደርቁ ሁሉ፣ እነርሱም ሆኑ ሀብታቸው የሚያልፉ ናቸውና፡፡
11
ፀሐይ በሚወጣ ጊዜ ሞቃታማ የሆነው ነፋስ ተክሎችን ያደርቃል፤ ደግሞም አበቦችን በምድር ላይ እንዲወድቁም ሆነ በውበታቸው እንዳይቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ባለ ጠጎች ልክ እንደሚሞቱ አበቦች ሁሉ ገንዘብን እየሰበሰቡ ሳሉ ይሞታሉ፡፡
12
በመከራ የሚጸኑትን ሰዎች እግዚአብሔር ያከብራቸዋል፤ ለሚወድዱት ሁሉ ተስፋ እንደ ሰጠው ለዘላለም እንዲኖሩ በማድረግ ብድራታቸውን ይከፍላቸዋል፡፡
13
በኃጢአት ስንፈተን እግዚአብሔር እየፈተነን ነው ብለን ልናስብ አይገባም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፉን እንድንሠራ አይፈልግምና፤ ክፉን እንዲያደርግ ማንንም አይፈትንምና፡፡
14
እያንዳንዱ ሰው የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲታለልና ሲሳብ ነው።
15
ክፉ ምኞት ከተፀነሰ በኋላ ኀጢአት ይወለዳል፤ ኀጢአትም ካደገች በኋላ ሞት ይወለዳል።
16
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ አትታለሉ።
17
ማንኛውም መልካምና ፍጹም ስጦታ እንደሚዘዋወር ጥላ ከማይለዋወጠው ከላይ ከሰማይ ከብርሃናት አባት ይወርዳል።
18
በፍጥረታቱ መካከል እንደ በኵራት እንድንሆን እግዚአብሔር በእውነት ቃል ሕይወት ሊሰጠን ወደደ።
19
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ይህን ዕወቁ። ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገዬ፣ ለመቆጣትም የዘገዬ ይሁን!
20
ምክንያቱም የሰው ቊጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያመጣም።
21
ስለዚህ ርኵሰትንና በየቦታው ሞልቶ ያለውን ክፋት አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁ የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ።
22
ለቃሉ ታዘዙ እንጂ፣ ሰሚዎች ብቻ በመሆን ራሳችሁን አታታልሉ።
23
ማንም ቃሉን እየሰማ ቃሉ የሚለውን ባያደርግ፣ ፊቱን በመስታወት እንደሚያይ ሰው ይሆናል።
24
ፊቱን አይቶ ይሄዳል፤ ምን እንደሚመስል ግን ወዲያው ይረሳዋል።
25
ፍጹሙንና ነጻ የሚያወጣውን ሕግ በጥንቃቄ የሚመለከትና የሚኖርበት እንጂ፣ ሰምቶ እንደሚረሳው ያልሆነ ሰው በሚያደርገው ሁሉ የተባረከ ይሆናል።
26
አንድ ሰው ሃይማኖተኛ ነኝ እያለ፣ አንደበቱን ግን ባይቆጣጠር፣ ልቡን ያስታል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው።
27
በእግዚአብሔር በአባታችን ፊት ንጹሕና ርኵሰት የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው፤ አባት የሌላቸውንና መበለቶችን በችግራቸው መርዳት፤ በዓለም ካለ ርኵሰት ራስን መጠበቅ።