ምዕራፍ 1

1 ዖዝያን፣ ኢዮአታም፣ አካዝና ሕዝቅያስ የይሁዳ ነገሥታት፣ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም ደግሞ የእስራኤል ንጉሥ በነበሩባቸው ዘመናት እግዚአብሔር ለሆሴዕ እነዚህን መልእክቶች ሰጠው፡፡ 2 እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ በነቢዩ በሆሴዕ በኩል በተናገረ ጊዜ፣ እንደዚህ አለ፡- ‹‹ሂድና አንዲት ዝሙት ዐዳሪ አግባ፤ ራስዋን ለሌሎች ወንዶች አሳልፋ ሰጥታ ስለ ነበረ፣ ልጆች ይኖሯታል፤ ዝሙት ዐዳሪዋን በምታገባበት ጊዜ ሕዝቤ በሚያሳፍር ሁኔታ ለእኔ ታማኝ ሳይሆኑ እንደ ቀሩ የሚያመለክት ይሆናል፡፡ ለእነርሱም እኔን አምላካቸውን እንዴት እንደተዉኝ የሚያመለክታቸው ይሆናል።›› 3 ስለዚህ ሆሴዕ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፡፡ እርሷም ፀነሰች ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ 4 እግዚአብሔር ሆሴዕን፣ ‹‹በኢይዝራኤል ከተማ ስለ ፈጸመው ግድያ የንጉሡን የኢዩን ቤተ ሰብ አባላት በቅርቡ ስለምቀጣ ለሕፃን ልጅህ ኢይዝራኤል የሚል ስም አውጣለት፤ የእስኤልም መንግሥት እንዲያከትም አደርጋለሁ፡፡ 5 በዚያን ቀን፣ በኢይዝራኤል ሸለቆ የእስራኤልን የውጊያ ዓቅም እደመስሳለሁ፡፡ 6 ጎሜር እንደ ገና ወዲያው ፀነሰችና ሴት ልጅ ወለደች፤ እግዚአብሔርም፣ ‹‹የእስራኤልን ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ ስለማልምራቸውና ካደረጓቸው ኃጢአቶች አንዱንም እንኳ ይቅር ስለማልልላቸው ልጅቷን ሎሩሐማ ብለህ ጥራት ትርጒሙም ‹ምሕረት ያላገኘች› ማለት ነው፡፡ 7 ለይሁዳ ሕዝብ ግን ምሕረት አደርጋለሁ፡፡ አድናቸዋለሁም የማድናቸው ግን በሚያጠፋ የጦር መሣሪያ፣ በቀስት፣ በሰይፍ ወይም በጦርነት አይደለም፡፡ በሠራዊት ወይም በብርቱ ፈረሶችና እነርሱን በሚጋልቧቸው አማካይነት አላድናቸውም፡፡ ይልቁንም እኔ እግዚአብሔር ራሴ አድናቸዋለሁ ብሎ ነገረው፡፡ 8 ሎሩሐማን ጡት ካስጣለች በኋላ ጎሜር እንደ ገና ፀነሰች ፤ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ 9 እግዚአብሔርም፣ ‹‹እስራኤል ሆይ፣ እናንተ ሕዝቤ ስላሆናችሁ፣ እኔም ከእንግዲህ ወዲያ አምላካችሁ ሆኜ ስለማልጠብቃችሁ፤ ልጁን ሎአሚ ብለህ ጥራው ትርጒሙም ‹ሕዝቤ አይደላችሁም› ማለት ነው፡፡ 10 በሚመጡ ዘመናት አንድ ቀን የእስራኤል ሕዝብ እንደ ባሕር አሸዋ ብዙ ይሆናሉ፤ ሊቈጥራቸው የሚችል ማንም አይኖርም፤ ለእስራኤል፣ ‹ሕዝቤ አይደላችሁም› ብዬአቸው ነበር፤ አንድ ቀን ግን፣ ‹‹የምጠብቃችሁና የምወዳችሁ ሕዝቤ ናችሁ›› እላቸዋለሁ፡፡ 11 በዚያ ቀን እግዚአብሔር የይሁዳን ሕዝብ ሁሉ ሰብስቦ ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ጋር በአንድነት ያመጣቸዋል፡፡ ከመካከላቸውም አንድ መሪ መርጠው በምርኮ ከተያዙበት ምድር ወጥተው ይሄዳሉ፡፡ በዚያ ቀን ‹‹የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሁን!› ይላሉ (ኢይዝራኤል ማለት ‹እግዚአብሔር ሕዝቡን ለምድራቸው ይተክላቸዋል› ማለት ነው)