ምዕራፍ 1
1
በሰው በኩል ወይም ከሰው ሳይሆን በክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞም እርሱን ከሞት ባስነሳው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆንኩት ጳውሎስ
2
አብረውኝ ካሉ ወንድሞች ጋር በገላትያ ለምትገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ
3
ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ
4
ይሁን፣እርሱ እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከአሁኑ ክፉ ዘመን ያድነን ዘንድ እራሱን ስለ ኃጢአታችን ሰጥቶአልና
5
ለእርሱ ከዘላለም እስከዘላለም ክብር ይሁን። አሜን!
6
ወደሌላ ወንጌል በዚህ ፍጥነት በመዞራችሁ እጅግ ተገርሜአለሁ። በክርስቶስ ጸጋ ከተጠራችሁ ከእርሱ ፊታችሁን ማዞራችሁ አስገርሞኛል።
7
ሌላ ወንጌል የለም፣ ነገር ግን የሚያውኩዋችሁና የክርስቶስን ወንጌል ሊያጣምሙ የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።
8
ነገር ግን እኛም ሆንን የሰማይ መልአክ አስቀድመን ከሰበክንላችሁ ሌላ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
9
አስቀድመን እንዳልን እንደገና እላለሁ « ማንም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገም ይሁን»
10
ለመሆኑ እኔ የምጥረው ከሰው ወይስ ከእግዚአብሔር ይሁንታን ለማግኘት ነው? ጥረቴ ሰውን ለማስደሰት ነው ? እስከአሁን ድረስ ሰውን ለማስደሰት እየጣርኩ ከሆነ እውነት እኔ የክርስቶስ አገልጋይ አይደለሁም።
11
ወንድሞች ሆይ የሰብኩላችሁ ወንጌል ከሰው እንዳልሆን እንድታውቁ እፈልጋለሁ።
12
ከጌታ ከኢየሱስ ከተሰጠኝ መገለጥ እንጂ ከሰው አልተቀበልኩትም ከሰውም አልተማርኩትም።
13
የይሁዲ እምነት ተከታይ በነበርኩበት በቀድሞው ህይወቴ ወቅት እንዴት ቤተክርስቲያንን በአመፅ አሳድድና አጠፋ እንደነበረ ስለእኔ ሰምታችኋል።
14
በይሁዲነት ከአብዛኛዎቹ አብረውኝ ከነበሩ አይሁዶች እየላቅሁ ነበር። ለአባቶቼም ወግ ከመጠን ያለፈ ቀናኢ ነበርኩ።
15
ነገር ግን እግዚአብሔር ገና በማህጸን ሳለሁ ሊመርጥኝ ወደደ፣
16
በአረማውያን መካከል አውጀው ዘንድ ልጁን በእኔ ለመግለፅ በጸጋው ጠራኝ። በጠራኝ ጊዜ ወዲያውኑ ከስጋና ከደም ጋር አልተማከርኩም
17
፣ከእኔ አስቀድመው ሃዋሪያት የሆኑት ወደሚገኙበት ወደ ኢየሩሳሌምም አልሄድኩም። ነገር ግን ወደ አረቢያ በኋላም ደግሞ ወደ መቄዶኒያ ተመለስኩ።
18
ከዚያም ከሶስት አመት በኋላ ኬፋን ለመጠየቅ ወደኢየሩሳሌም ሄጄ ከእርሱ ጋር አስራአምስት ቀናት ቆየሁ።
19
ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በስተቀር ሌሎች ሃዋሪያትን አላገኘሁም።
20
በምፅፍላችሁ በእነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር ፊት እንዳልዋሸሁ እወቁ።
21
ቀጥሎም ወደ ሶሪያና ኪልቂያ አውራጃዎች ሄድኩኝ።
22
እስከዚያን ጊዜ ድረስ በይሁዳ ላሉት አብያተክርስቲያናት በአካል አልታወቅም ነበር፣
23
ነገር ግን «ያ ቀድሞ ያሳድደን የነበረው ሰው አሁን ሊያጠፋው ሲጥር የነበረውን እምነት እየሰበከ ነው» የሚል ወሬ ብቻ ይሰሙ ነበር፣
24
ስለ እኔም እግዚአብሔርንም ያከብሩ ነበር።