ምዕራፍ

1 እያንዳንዳቸው ቤተ ሰባቸውን በመያዝ፣ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፦ 2 ሮሜል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ 3 ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ብንያም፣ 4 ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድና አሴር። 5 ከያዕቆብ ዘር የተገኙት ሰዎች ሰባ ነበር። ዮሴፍ ቀድሞውኑ በግብፅ ውስጥ ነበረ። 6 ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ፣ ወንድሞቹ ሁሉና ያ ትውልድ በሙሉ ሞቱ። 7 ነገር ግን እስራኤላውያን እየተዋለዱ ሄዱ፤ ቊጥራቸውም እጅግ ጨምሮ በጣም ብርቱዎች ሆኑ፤ ምድሪቱንም ሞሏት። 8 በግብፅ ስለ ዮሴፍ የማያውቅ ዐዲስ ንጉሥ ተነሣ። 9 ለሕዝቡም እንደዚህ አለ፤ “እስራኤላውያንን ተመልከቷቸው፤ ከእኛ ይልቅ በቍጥር በዝተዋል፤ እጅግም በርትተዋል። 10 በቍጥር እየበዙ እንዳይሄዱ፣ ጦርነት ቢነሣም ከጠላቶቻችን ጋር ዐብረው እንዳይወጉንና ምድሪቱ ጥለው እንዳይሄዱ ኑ በዘዴ እርምጃ እንውሰድባቸው።” 11 በከባድ ሥራ የሚያስጨንቋቸው አሠሪ አለቆችን በላያቸው ሾሙ። እስራኤላውያን ለፈርዖን ፊቶምና ራምሴ የተባሉ የንብረት ማከማቻ ከተሞችን ሠሩ። 12 ግን ግብፃውያን እስራኤላውያንን ባስጨነቋቸው ቊጥር፣ እስራኤላውያን በቊጥር እየበዙና በምድሪቱ እየተስፋፉ ሄዱ። ስለዚህ ግብፃውያን እስራኤላውያን መፍራት ጀመሩ። 13 ግብፃውያን እስራኤላውያንን በጥብቅ እንዲሠሩ አደረጓቸው። 14 በሸክላ ሥራና ጭቃ በማስቦካት፣ በዕርሻ ውስጥም ሁሉን ዐይነት ከባድ ሥራ በማሠራት አስመረሯቸው (ሕይወታቸውን መራራ አደረጉባቸው)። የሚጠበቅባቸው ሥራ ሁሉ ከባድ ነበር። 15 ከዚያም በኋላ የግብፅ ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የሚባሉ ዕብራውያት አዋላጆችን እንዲህ አላቸው፤ 16 “ዕብራውያት ሴቶችን በማማጫው ላይ ስታዋልዱ፣ በሚወልዱበት ጊዜ ተመልከቱ። ወንድ ከተወለደ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” 17 ነገር ግን አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ፈሩ፣ ንጉሡ ያዘዛቸውንም አልፈጸኩም፤ ትእዛዙን በመፈጸም ፈንታ ሕፃናት ወንዶችን በሕይወት እንዲኖሩ አደረጉ። 18 የግብፅ ንጉሥ አዋላጆቹን ጠርቶ፣ “ለምን ይህን አደረጋችሁ፣ ሕፃናት ወንዶችንስ ለምን አልገደላችኋቸውም?” አላቸው። 19 አዋላጆቹም ለፈርዖን፣ “ዕብራውያት ሴቶች እንደ ግብፃውያት ሴቶች አይደሉም። እነርሱ ብርቱዎች ናቸው፣ የሚወልዱትም አዋላጅ ወደ እነርሱ ከመምጣቱ በፊት ነው” በማለት መለሱለት፥ 20 እግዚአብሔር እነዚህን አዋላጆች ጠበቃቸው። ሕዝቡ በቍጥር በዙ፣ እጅግ ብርቱዎችም ሆኑ። 21 አዋላጆቹ እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ፣ እግዚአብሔር ቤተ ሰቦችን ሰጣቸው። 22 ፈርዖን፣ “የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወንዝ ውስጥ ጣሉ፣ ሴትን ልጅ ግን በሕይወት እንድትኖር ታደርጋላችሁ” በማለት ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።