ምዕራፍ

1 ንጉስ ጠረክሲስ 127 አውራጃዎች ያሉትን ትልቅ ግዛት ያስተዳድር ነበር፡፡ ግዛቱ በምስራቅ እስከ ህንድ በምዕራብ እስከ ኢትዮጵያ ይደርስ ነበር፡፡ 2 ግዛቱን ያስተዳድር የነበረው እጅግ በተመሸገው በሱሳ ከተማ ተቀምጦ ነበር፡፡ 3 በነገሰ በሶስተኛው ዓመት፣ ለአስተዳዳሪዎቹና ለሌሎች ሹማምንቱ ሁሉ ግብዣ አደረገላቸው፡፡ የፋርስንና የሜዶን ሰራዊቶችን ወደ ድግሱ እንዲመጡ ጋበዘ፡፡ እንደዚሁም የየአውራጃዎቹን ገዥዎችና መሪዎች ጋብዟቸው ነበር፡፡ 4 ክብረ በዓሉ ለ180 ቀናት ተካደ፡፡ በእነዚያ ጊዜያት ንጉሱ ለእንግዶቹ መንግስቱን ታላቅ የሚያሰኘውን የሃብቱን ብዛትና ሌሎች ነገሮች አሳያቸው፡፡ 5 በግብዣው ፍጻሜ፣ ንጉሱ ህዝቡን ለሌላ ክብረ በዓል ጠራ፡፡ ታላላቆችንና ታናናሾችን ጨምሮ በቤተ መንግስቱ የሚያገለግሉትን ሁሉ ወደ ግብዣው ጠራ፡፡ ክብረ በዓሉ ሰባት ቀናት ተደረገ፡፡ ግብዣው የተደረገው በቤተ መንግስቱ መናፈሻ አደባባይ ነበር፡፡ 6 የመናፈሻው አደባባይ በሀምራዊ የተልባ እግር ጨርቅ በተሰራ ገመድ በብር ቀለበቶች በእምነበረድ አምዶች ላይ በተንጠለጠሉ ነጭና ሀምራዊ መጋረጃዎች አጊጦ ነበር፡፡ ከጌጣጌጥ መስሪያ ውድ አለቶች፣ ከእምነበረድ፣ ከዛጎልና ሉል እንዲሁም ከሌሎች የከበሩ ድንጋዮች በተሰሩ ወለሎች ላይ በወርቅና ብር ያጌጡ መከዳዎች ነበሩ፡፡ 7 እንግዶቹ በወርቅ በተሰራ ዋንጫ ወይን ይጠጡ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ዋንጫ በላዩ ላይ የተለያዩ ምልክቶች ነበሩት፡፡ ንጉሱ የተትረፈረፈ ወይን አቅርቦ ስለነበር እንግዶቹ ብዙ የሚጠጡት ነበራቸው፡፡ 8 ንጉሱ እንግዶቹ የፈለጉትን ያህል እንዲጠጡ ይፈልግ ስለነበር እጅግ ብዙ ወይን ጠጅ ተዘጋጅቶ ነበር፤ ነገር ግን ህጉ፣ “ማንም ሰው ለመጠጣት አይገደድም” የሚል ነበር፡፡ 9 ንግስት አስጢንም በቤተ መንግስቱ በሌላ ስፍራ ሴቶችን ለግብዣ ጠርታ ነበር፡፡ 10 በእነዚያ የግብዣ ጊዜያት በሰባተኛው ቀን፣ ንጉሱ ጠረክሲስ ወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ በተሰኘ ጊዜ ግላዊ ፍላጎቶቹንና መሻቶቹን ከሚያማክራቸው ከሰባቱ አገልጋዮቹ ከምሁማ፣ ባዛን፣ ሐርቦና፣ ገበታ፣ ዘቶልያ፣ ዜታርና ከርከስን ጋር ተነጋገረ፡፡ 11 ንግስት አስጢን ምን ያህል ውብ እንደሆነች እንግዶቹ እንዲያዩ ፈልጎ፣ ዘውዷን ጭና ወደ እርሱ እንዲያመጧት አዘዛቸው፡፡ 12 ንግስት አስጢን ግን ወደ ንጉስ መሄድ አልፈቀደችም፡፡ አገልጋዮቹ ከንጉሱ ያመጡትን ትዕዛዝ ለመቀበል አልወደደችም፡፡ ይህ ንጉሱን በጣም አስቆጣው፡፡ 13 ስለዚህ ንጉሱ ስለ እነዚህ አይነት ነገሮች ህጉንና መሆን የሚገባውን ከሚያውቁ ጠቢባን ጋር ተነጋገረ፡፡ 14 እነዚህምአማካሪዎቹ የሆኑት የፋርስና ሜዶን ሰባቱ ልዑላን፤ አርቄስዮስ፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሺሽ፣ ሜሬስ፣ ማሌሴዓር እና ምሙካ ናቸው፡፡ እነዚህ በመንግስቱ ከፍተኛውን ስልጣን የያዙ ሲሆኑ፣ እነርሱ ሲናገሩ ንጉሱ ለምክራቸው ትኩረት ይሰጣል፡፡ 15 ንጉሱ እንዲህ አላቸው፣ “ንግስት አስጢን ወደዚህ እንድትመጣ አገልጋዮቼን ብልካቸውም እርሷ ግን እኔን መታዘዝ አልፈቀደችም፡፡ እንደዚህ ባደረገ ላይ ህጋችን ምን ይደረግበት ይላል?” 16 ሌሎቹም ሹማምንት በተገኙበት ምሙካ እንዲህ አለ፣ “ግርማዊ ሆይ፣ ንግስት አስጢን አንተን ሰድባለች፣ እንዲሁም ግርማዊ በምትገዛበት አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙ ሹማምንትን ሁሉ ሰድባለች፡፡ 17 በግዛትህ የሚገኙ ሴቶች እርሷ የተናገረችውን ይሰማሉ፣ እናም እንዲህ ይላሉ፣ ‘ንጉሱ ንግስት አስጢንን ወደ እርሱ ሲያስጠራት፣ እርሷ ግን መሄድ አልፈለገችም፡፡’ ስለዚህ እነርሱም ባሎቸውን አይታዘዙም፣ ለባሎቸው ንቀት ያሳያሉ፡፡ 18 ይህች ቀን ሳታልፍ፣ በፋርስና ሜዳን ያሉ የሹማምንቱ ሚስቶች ሁሉ ንግስቲቱ ያለችውን ይሰማሉ፣ ለግርማዊነትህ ሹማምንት ሚስቶቻቸው ንግስቲቱ ያለችውን ይናገራሉ፡፡ ለወንዶች ሁሉ ንቀትና ቁጣ ያሳያሉ፡፡ 19 ስለዚህ ግርማዊነትህን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ፣ እንደ ፋርስና ሜዶን ህግ ማንም ሊቀይረው የማይችል የጸና ህግ አውጣ፡፡ ይህም ንግስት አስጢን ፊትህን ደግማ ማየት የማትችል መሆኗንና አንተ ከእርሷ ይልቅ የተሻለች ንግስት መሆን የሚገባትን ሴት እንድምትመርጥ የሚገልጽ ይሁን፡፡ 20 በግዛትህ የሚኖር ሁሉ የሰጠኸውን ትዕዛዝ ሲሰማ፣ የታላላቆቹም ሆነ የታናናሾቹ ሰዎች ሚስቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ፡፡” 21 ንጉሱና ሹማምንቱ የምሙካ አሳብ ደስ አሰኛቸው፣ ንጉሱም ምክሩን አጸና፡፡ 22 ንጉሱ ወደየአውራጃዎቹ ሁሉ ወንዶች ሁሉ በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ ሙሉ ስልጣን ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚገልጽ ደብዳቤ ላከ፡፡ ደብዳቤዎቹን በእያንዳንዱ ቋንቋና በየተላከበት አውራጃ በየራሳቸው ጽሁፍ ላከ፡፡