ምዕራፍ 1
1
በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፥ ለእግዚአብሔር ለተለዩት በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑ በኤፌሶን ለሚኖሩ ቅዱሳን፤
2
ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3
በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ።
4
እግዚአብሔር በክርስቶስ የምናምነውን እኛን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት መርጦናል። ይህም በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ ነው
5
እግዚአብሔር በፍቅር በኢየሱስ ክርስቶስ የራሱ ልጆች አድርጎ ሊቀበለን አስቀድሞ ወሰነን። ይህንንም የፈጸመው ሊያደርግ የፈለገውን ነገር ለማድረግ ደስ ስለተሰኘ ነበር።
6
ይህ ሁሉ የተፈጸመው በሚወደው ልጁ እንዲያው በነጻ ስለ ተሰጠን ክቡር ጸጋው እግዚአብሔር ይመሰገን ዘንድ ነው።
7
እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን በሚወደው ልጁ ደም ቤዛነትን ይኸውም የሐጢአት ይቅርታን አገኘን።
8
ይህም ጸጋ በጥበብና በማስተዋል ሁሉ ተትረፍርፎ ተሰጠን።
9
በክርስቶስ በተገለጠው ፈቃዱ መሠረት እግዚአብሔር በዕቅዱ ውስጥ ያለውን የተሰወረውን እውነት እንድናውቅ አድርጎናል፤
10
ዕቅዱን የሚፈጽምበት ጊዜ ሲድርስ በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በአንድ ላይ በክርስቶስ ስር ይጠቀልላል።
11
ሁሉንም ነገር እንደ ገዛ ፈቃዱ በሚያደርገው ዕቅድ መሠረት በክርስቶስ ተመረጥን፤ አስቀድሞም ተወሰንን
12
ይህም የሆነው በክርስቶስ በማመን ቀዳሚ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና ይሆን ዘንድ እንድንኖር ነው።
13
ባመናችሁበትና እንደ ተሰጠው ተስፋ በመንፈስ ቅዱስ በታተማችሁበት በክርስቶስ አማካይነት የመዳናችሁ ወንጌል የሆነውን የእውነት ቃል የሰማችሁት በክርስቶስ ነው
14
ለክብሩ ምስጋና እንዲሆን ተስፋ የተደረገው ሀብት በእጅ እስገሚገባ ድረስ መንፈስ ቅዱስ የርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው።
15
ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለእርሱም ቅዱሳን ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ
16
ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ማመስገንና እናንተንም በጸሎቴ ማስታወስ አላቋረጥሁም ።
17
የክብር አባት፥የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን ለማወቅ የሚያስችላችሁን የጥበብ እና የመገለጥ መንፈስ እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤
18
የምጸልየውም የመጠራታችን አስተማማኝነት እና በእርሱ ቅዱሳን መካከል የርስቱ ክብር ባለጠግነት ምን እንደሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
19
እንዲሁም እንደ ኀይሉ ብርታት አሠራር በእኛ በምናምነው ውስጥ የሚሠራው የኀይሉ ታላቅነት ምን እንደሆነ እንድትረዱ ነው።
20
ይህም እግዚአብሔር ከሙታን ባስነሳውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ እንዲቀመጥ ባደረገው ጊዜ በክርስቶስ ውስጥ የታየው ኀይል ነው።
21
ክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በአብ ቀኝ የተቀመጠውም ከማንኛውም ግዛት፥ ሥልጣን፥ኀይልና ጌትነት እንዲሁም በዚህ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ሊሰየም ከሚችለው ስም ሁሉ በላይ ነው።
22
እግዚአብሔር ሁሉም ነገር በክርስቶስ እግር ሥር እንዲገዛ አድርጓል፤ እርሱንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሁሉም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾሞታል
23
ቤተ ክርስቲያንም ሁሉንም ነገር በሁሉም መንገድ የሚሞላው የእርሱ ሙላት የሆነች አካሉ ናት።