ምዕራፍ 1

1 ይህ በኢየሩሳሌም የነገሠውና የዳዊት ልጅ የሆነው የአስተማሪው ቃል ነው። 2 አስተማሪው እንዲህ ይላል፥ "እንደ እንፋሎት ትነት፥ በደመናም ውስጥ እንዳለ እስትንፋስ፥ ሁሉም ነገር ይጠፋል፥ በርካታ ጥያቄዎችን ትቶ። 3 ከፀሐይ በታች በሚደክሙበት ሥራ ሁሉ የሰው ልጆች ምን ትርፍ ያገኙበት ይሆን? 4 አንደኛው ትውልድ ይሄዳል፥ ሌላኛው ትውልድ ይመጣል፥ ምድር ግን ለዘላለም ትኖራለች። 5 ፀሐይ ትወጣለች፥ ትጠልቃለችም፥ ዳግም ወደምትወጣበት ሥፍራ ለመመለስም ትቸኩላለች። 6 ነፋስ ወደ ደቡብ ይነፍሳል፥ ወደ ሰሜንም ያከብባል፥ ሁሌም በመንገዱ ይሄዳል፥ እንደገናም ይመለሳል። 7 ወንዞች ሁሉ ወደ ባህር ይፈስሳሉ፥ ባህሩ ግን መቼም ቢሆን አይሞላም። ወንዞቹ ወደሚሄዱበት ሥፍራ፥ ወደዚያው ሥፍራ እንደገና ይሄዳሉ። 8 ሁሉም ነገር አድካሚ ነው፥ ሊያስረዳ የሚችልም የለም። ዓይን በሚያየው አይረካም፥ ጆሮም በሚሰማው አይሞላም። 9 የሆነው ሁሉ ወደፊትም የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ሁሉ ወደፊት የሚደረግ ነው። ከፀሐይ በታች አንድም አዲስ ነገር የለም። 10 'ተመልከት፥ ይህ አዲስ ነው' ሊባልለት የሚችል አንዳች ነገር አለ? አሁን ያለው ሁሉ ለብዙ ዘመናት አስቀድሞ የነበረ ነው፥ ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት በዘመናት መካከል። 11 በቀድሞ ዘመን የሆኑትን ነገሮች የሚያስታውስ ያለ አይመስልም። እጅግ ዘግይተው የሆኑትን ነገሮችና ወደፊት ሊሆኑ ያሉት ሁለቱም የሚታወሱ አይመስሉም። 12 እኔ አስተማሪ ነኝ፥ በእስራኤልም ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርኩ። 13 ከሰማይ በታች የተደረገውን ነገር ሁሉ በጥበብ ለማጥናትና ለመመርመር አዕምሮዬን አሠራሁት። ይህ ምርምር እግዚአብሔር የሰው ልጆች በሥራ እንዲጠመዱ የሰጣቸው አድካሚ ተግባር ነው። 14 ከሰማይ በታች የተሠሩትን ሥራዎች ሁሉ አየሁ፥ ተመልከቱ፥ ሁሉም የሚተንና ነፋስን ለማገድ መሞከር ነው። 15 የተጣመመ መቃናት አይችልም! የጠፋው መቆጠር አይችልም! 16 ለልቤ እንዲህ ስል ተናገርኩ፥ "ተመልከት፥ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አከማችቻለሁ። አዕምሮዬ ትልቅ ጥበብንና እውቀትን አይቷል።" 17 ስለዚህ ጥበብን ለማወቅ ልቤን አሠራሁት፥ ደግሞም ዕብደትንና ሞኝነትን። ይህም ደግሞ ነፋስን ለማገድ እንደ መሞከር መሆኑን አስተዋልኩኝ። 18 ጥበብን በማብዛት ውስጥ ብዙ ተስፋ መቁረጥ አለ፥ እውቀትንም የሚያበዛ ሐዘንን ያበዛል።