ምዕራፍ 1

1 በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት በሦሥተኛው ዓመት፥አቅርቦቶቿን ሁሉ ለማስቆም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ከበባትም። 2 ጌታም ለናቡከደነፆር በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአቄም ላይ ድል ሰጠው፥እርሱም ከእግዚአብሔር ቤት የተቀድሱ ዕቃዎች ጥቂቱን ሰጠው። እርሱም ወደ ባቢሎን ምድር፥ ወደ አምላኩ ቤት አመጣቸው፥የተቀደሱትንም ዕቃዎች በአምላኩ ግምጃ ቤት ውስጥ አኖራቸው። 3 ንጉሡም ዋና አለቃውን አስፋኔዝን፥ ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ቤተስብ የሆኑትን፥ ከእስራኤል ሰዎች አንዳንዶችን፦ 4 ነውር የሌለባቸውን ወጣት ወንድች፥ መልከ መልካሞችን፥ ጥበበኞችን፥ በዕውቀትና በማስተዋል የተሞሉትንና በንጉሡ ቤት ለማገልገል ብቁዎች የሆኑትን እን ዲያመጣ ተናገረው። የባቢሎናውያንን ሥነ ጽሑፍና ቋንቋ እንዲያስተምራቸው ተናገረው። 5 ንጉሡ ከምግቡና ከሚጠጣው ወይን በየዕለቱ ድርሻ መደበላቸው። እነዚህ ወጣት ወንዶች ለሦሥት ዓመት መሠልጠንና ከዚያ በኋላ ንጉሡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። 6 ከእነዚህም መካከል አንዳንድ የይሁዳ ሰዎች፥ ዳንኤል፥ አናንያ፥ ሚሳኤልና አዛሪያ ነበሩ። 7 ዋና አለቃውም ስም አወጣላቸው፦ ዳንኤልን ብልጣሶር፥ አናንያን ሲድራቅ፥ ሚሳኤልን ሚሳቅ፥ አዛሪያንም አብድናጎ ብሎ ጠራቸው። 8 ነገር ግን ዳንኤል በንጉሡ ምግብና በሚጠጣውም ወይን ራሱን እንዳያረክስ በውስጡ አሰበ። ራሱን እንዳያረክስ ከዋናው አለቃ ፈቃድ ጠየቀ። 9 ዋና አለቃው ለእርሱ ባለው አክብሮት አማካይነት እግዚአብሔር ለዳንኤል ሞገስንና ጸጋን ሰጠው። 10 ዋና አለቃውም ዳንኤልን አለው፥ « እኔ ጌታዬን ንጉሥን እፈራለሁ። ምን ዓይነት ምግብና መጥጥ ማግኘት እንዳለባችሁ አዞኛል። በእናንተ እድሜ ካሉ ወጣቶች ይልቅ ከስታችሁ ስለ ምን ይመለከታል? ንጉሡ ከእናንተ የተነሳ በሞት ይቀጣኝ ይሆናል።» 11 ዳንኤልም ዋናው አለቃ በዳንኤል፥በአናንያ፥በሚሳኤልና በአዛሪያ ላይ ለሾመው መጋቢ ተናገረ። 12 እርሱም አለ፥«እባክህ፥እኛን አገልጋዮችህን ለአሥር ቀናት ፈትነን። የምንመገብው ጥቂት አትክልትና የምንጠጣው ውኃ ብቻ ስጠን። 13 ከዚያም የእኛን ፊት የንጉሡን ምግብ ከሚመገቡ ወጣቶች ጋር አስተያይ፥ባየኽውም መሠረት በአገልጋዮችህ ላይ አድርግ።» 14 መጋቢውም ይህን ለማድረግ ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ለአሥር ቀናትም ፈተናቸው። 15 ከአሥርም ቀን በኋላ የንጉሡን መብል ከተመገቡ ወጣቶች ይልቅ ጤነኞችና የተሻለ የተመገቡ ሆነው ታዩ። 16 ስለዚህ መጋቢው የተመደበላቸውን የተመረጠ ምግብና ወይን አስቀርቶ አትክልት ብቻ ሰጣቸው። 17 ለእነዚህ አራት ወጣቶች፥ እግዚአብሔር በሁሉም ሥነ ጽሑፍና በጥበብ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፥ ዳንኤልም ሁሉንም ዐይነት ራዕይና ሕልም መረዳት ይችል ነበር። 18 እንዲያስገቡአቸው ንጉሡ የመደበው ጊዜ እንዳበቃ፥ዋናው አለቃ በናቡከደነፆር ፊት አቀረባቸው። 19 ንጉሡም ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ፥አብረዋቸው ከነበሩት ሁሉ መካከል ከዳንኤል፥ሐናንያ፥ ሚሳኤልና አዛርያ ጋር የሚወዳድር ማንም አልነበረም። በንጉሡ ፊት ቆሙ፥ ሊያገለግሉት ዝግጁዎች ነበሩ። 20 ንጉሡ በጠየቃቸው የጥበብና የማስተዋል ጥያቄዎች ሁሉ፥በግዛቱ ሁሉ ከሚገኙ አስማተኞችና ሙታን ሳቢዎች አሥር እጥፍ በልጠው ተገኙ። 21 ዳንኤልም እስከ ንጉሥ ቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት ድረስ እዚያው ነበረ።