ምዕራፍ 1
1
በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቲዎስ፤
2
በቆላስይስ ለሚኖሩ ለእግዚአብሔር ለተለዩና በክርስቶስ ታማኝ ለሆኑ አማኞች፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ጸጋና ሰላም ይሁንላችሁ።
3
ለእናንተ በምንጸልይበት ጊዜ ሁሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔርን እናመሰግናለንን።
4
በክርስቶስ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነትና ለእግዚአብሔር ለተለዩት ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተናል።
5
በሰማይ ከተጠበቀላችሁ ከመታመነ ተስፋ የተነሣ ይህ እምነትና ፍቅር አላችሁ። ስለዚህም ተስፋ በወንጌል የእውነት ቃል አስቀድማችሁ ሰማችሁ፤ ይህም ወደ እናንት ደርሶአል።
6
ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በእናንተም ዘንድ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው።
7
በእኛ ምትክ ለእናንተ የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነውና ከእኛም ጋር አብሮን ከሚያገለግል ከተወዳጁ ከኤጳፍራ ይህን ተምራችኋል።
8
ደግሞም በእግዚአብሔር መንፈስ ያላችሁን ፍቅር ነግሮናል።
9
ከዚህም ፍቅር የተነሣ ስለ እናንተ ከሰማንበት ቀን ጀምሮ ለእናንተ ከመጸለይ አላቋረጥንም። በፈቃዱ ዕውቀት፣ በጥበብ ሁሉና በመንፈሳዊ ማስተዋል እንድትሞሉ እንጸልይላችኋለን።
10
ጌታን ደስ በሚያሰኝ መንገድ በሁሉም እንደሚገባ እንድትመላለሱ፤ በማናቸውንም መልካም ሥራ ፍሬ እንድታፈሩና በእግዚአብሔርም ዕውቀት እንድታድጉ እንጸልያለን።
11
በሁሉም ነገር እንድትጽኑና ትእግሥት እንዲኖራችሁ ፣ከኅይሉ ክብር የተነሣም በሁሉ ብርታትና ጥንካሬ እንዲኖራችሁ እንጸልያለን።
12
በብርሃን ከሚኖሩት አማኞች ጋር የርስቱ ተካፋይ እንድንሆን ላበቃን ለእግዚአብሔር በደስታ ምስጋና ማቅረብ እንድትችሉ እንጸልያለን።
13
ከጨለማ ኅይል አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ወደ ልጁ መንግሥት አሸጋገረን።
14
በልጁም የኅጢአታችንን ይቅርታ፣ ድነትን አገኘን።
15
ልጁ የማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው። እርሱ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው።
16
ምክንያቱም በሰማያትና በምድር፤ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋል። ዙፋናትም ሆኑ ኅይላት ወይም ግዛቶችች ወይም ሥልጣናት፤ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥረዋል።
17
እርሱ ከሁሉ በፊት ነበረ፤ሁሉም ነገር የተያያዘው በእርሱ ነው።
18
እርሱ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱ የሁሉም መገኛና የሁሉም የመጀመሪያ፣ከሙታንም በኩር ነው።
19
በመሆኑም በሁሉም ነገሮች መካከል የመጀመሪያ ነው። በእርሱ የእግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ እንዲኖርና እግዚአብሔር በልጁ በኩል ሁሉን ነገር
20
ከራሱ ጋር ያስታርቅ ዘንድ ስለ ወደደ ነው። እግዚአብሔር ልጁ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም በሰማያትም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ አስታረቀ።
21
እናንተም ቀድሞ ከእግዚአብሔር ርቃችሁ ነበር፤ በአሳባችሁና በክፉ ሥራችሁም ምክንያት ጠላቶች ነበራችሁ።
22
አሁን ግን ቅዱሳንና ንጹሓን፤ ነቀፋም የሌለባችሁ አድርጎ በፊቱ ሊያቀርባችሁ በልጁ ሞት እግዚአብሔር ከራሱ ጋር አስታረቃችሁ። ይህም በእርሱ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በወንጌሉ ከተገኘው ተስፋ ሳትናወጡ
23
በእምነት ጸንታችሁ እንድትኖሩ ነው። ይህም ወንጌል እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ ተሰብኮአል። እኔም ጳውሎስ አገልጋይ የሆንኩት ለዚህ ወንጌል ነው።
24
አሁን ስለ እናንተ በምቀበለው መከራ ደስ ይለኛል። አካሉ ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያንም ከክርስቶስ መከራ ከመካፈል የጎደለውን በሥጋዬ አሟላለሁ።
25
የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ለእናንተ እንድገልጥ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ኅላፊነት ቃሉን ለመፈጸም የማገለግለው ይህችን ቤተ ክርስቲያን ነው።
26
ይህም ባለፉት ዘመናትና ትውልዶች ከሰው ልጆች ተሰውሮ የቆየውና አሁን ግን እግዚአብሔር ለሚያምኑት ሁሉ የገለጠው ምስጢር ነው።
27
እግዚአብሔርም በእናንተ መካከል ለአሕዛብ ሊገልጥላቸው የፈለገው የዚህ ምስጢር የክብር ብልጽግና ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ነው። ይህም ምሥጢር በተስፋ የምንጠባበቀው ክብር የሚገኝበት ክርስቶስ በእናንተ መካከል መሆኑ ነው።
28
የምንሰብከው እርሱን ነው። እያንዳንዱን ሰው በክርስቶስ ፍጹም አድርገን ለማቅረብ ጥበብን ሁሉ በማስተማርና በመምክር ሰውን ሁሉ እንገስጻለን።
29
በውስጤ በኅይል በሚሠራው መሠረት በብርቱ እየታገልኩ እደክማለሁ።