1 ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ፣ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር። 2 ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚገቡ ሰዎች ምጽዋት መለመን እንዲችል፣ ውብ ተብሎ በሚጠራው በቤተ መቅደሱ በር ላይ ሰዎች በየቀኑ በሸክም አምጥተው የሚያስቀምጡት፣ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ዐንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። 3 ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ቤተ መቅደሱ ሊገቡ ሲሉ ባያቸው ጊዜ፣ ምጽዋት ለመነ። 4 ጴጥሮስ ዐይኖቹን ምጽዋት በሚለምነው ሰውዬ ላይ በማድረግ፣ ከዮሐንስ ጋር “ወደ እኛ ተመልከት” አለው። 5 ዐንካሳውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለመቀበል በመጠበቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። 6 ጴጥሮስ ግን፣ “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ። በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተራመድ” አለው። 7 ጴጥሮስ ቀኝ እጁን ያዘውና ወደ ላይ አነሣው፤ ወዲያውም እግሮቹና የቍርጭምጭሚቱ ዐጥንቶች ጥንካሬ አገኙ። 8 ዐንካሳው ሰውዬ ወደ ላይ ዘልሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ጋርም እየተራመደ፣ እየዘለለና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። 9 ሰዎች ሁሉ ዐንካሳው እየተራመደ ሲሄድና እግዚአብሔርን ሲያመሰግን አዩት። 10 ምጽዋት ለመቀበል ውብ በሚባለው የቤተ መቅደሱ በር ላይ ይቀመጥ የነበረው ሰውዬ እንደ ሆነም ዐወቁ፤ በእርሱ ላይ ከሆነው የተነሣም በመደነቅና በመገረም ተሞሉ። 11 ሰውየው የጴጥሮስንና የዮሐንስን እጅ ይዞ ሳለ፣ የሰሎሞን መመላለሻ በሚባለው ደጅ ሰዎች ሁሉ በኀይል እየተደነቁ በአንድነት ወደ እነርሱ ሮጡ። 12 ጴጥሮስ ይህን ሲያይ ለሕዝቡ፣ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ለምን ትደነቃላችሁ? ይህን ሰው በገዛ ኀይላችን ወይም በመንፈሳዊነታችን እኛ እንዲራመድ እንዳደረግን ሁሉ፣ ለምን ዐይናችሁን አፍጥጣችሁ ትመለከታላችሁ? በማለት መልስ ሰጠ። 13 የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ፣ የአባቶቻችን አምላክ አገልጋዩን ኢየሱስን አክብሮታል። እርሱ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትና ጲላጦስ ሊፈታው ወስኖ ሳለ፣ በፊቱ የካዳችሁት ነው። 14 ቅዱሱንና ጻድቁን ካዳችሁት፤ በእርሱም ፈንታ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ። 15 እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣውን፣ የሕይወትን ጌታ ገደላችሁት፤ እኛም የዚህ ምስክሮች ነን። 16 በእርሱ ስም ማመን አሁን የምታዩትንና የምታውቁትን ይህን ሰው ብርቱ አድርጎታል። አዎ፣ በኢየሱስ ያለው እምነቱ በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤንነት ሰጠው። 17 አሁን ወንድሞች ሆይ፣ አለቆቻችሁም እንዳደረጉት ባለማወቅ ያደረጋችሁት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። 18 ነገር ግን እግዚአብሔር በነቢያቱ ሁሉ አፍ የእርሱ ክርስቶስ መከራ መቀበል እንዳለበት አስቀድሞ የተናገረውን አሁን ፈጸመው። 19 እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ፣ ከጌታ ዘንድም የመታደስ ዘመን እንዲመጣ ንስሓ ግቡ፤ ተመለሱም፤ 20 ይኸውም ለእናንተ የመረጠውን ክርስቶስ የሆነውን ኢየሱስን እንዲልከው ነው። 21 እርሱ ሰማያት ሊቀበሉትና ነገሮች ሁሉ እስከሚታደሱበት ዘመን ድረስ ጠብቀው ሊያቈዩት የሚገባ፣ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተነገረለት ነው። 22 ሙሴ በእርግጥ፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣል። የሚነግራችሁንም ሁሉ ስሙ’ አለ። 23 ያን ነቢይ የማይሰማ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። 24 አዎ፣ ከሳሙኤል ጀምሮና ከእርሱም በኋላ የተናገሩ ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ቀኖች ተናግረዋል። 25 እናንተ የነቢያትና ‘በዘርህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ ለአብርሃም እንደ ተናገረው፣ ከአባቶቻችሁ ጋር እግዚአብሔር ያደረገው ኪዳን ልጆች ናችሁ። 26 እግዚአብሔር አገልጋዩን ካስነሣ በኋላ በመጀመሪያ ወደ እናንተ ላከው፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ መልሶ ሊባርካችሁ ነው።