1 አይሁዶች የበዓለ ሀምሳን በዓል በሚያከብሩበት ቀን፣ አማኞች በኢየሩሳሌም በአንድ ስፍራ አብረው ነበሩ፡፡ 2 በድንገት እንደ ሀይለኛ ነፋስ ከሰማይ የሚመጣ ድምጽ ሰሙ፡፡ ተቀምጠውበት በነበረው ቤት ውስጥ የነበሩ ሁሉ ድምጹን ሰሙ፡፡ 3 ከዚያ የእሳት ነበልባል የሚመስል ተመለከቱ፡፡ እነዚህ ነበልባሎች እርስ በእርሳቸው እየተከፋፈሉ፣ እያንዳንዱ ነበልባል በእያንዳንዱ አማኝ ራስ ላይ ወረደ፡፡ 4 ከዚያ መንፈስ እያንዳንዳቸውን እንዳስቻላቸው ሁሉም አማኞች በመንፈስ ቅዱስ እየተሞሉ የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር ጀመሩ፡፡ 5 በዚያን ጊዜ ብዙ አይሁዶች የበአለ ሀምሳን በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም ነበሩ፡፡ እነርሱ ሁልጊዜም እግዚአብሔርን የሚያመልኩ የአይሁድ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከተለያዩ ብዙ አገሮች የመጡ ነበሩ፡፡ 6 እንደ ነፋስ የሆነውን ከፍተኛ ድምፅ ሲሰሙ፣ አማኞቹ ወደነበሩበት ስፍራ ብዙ ሆነው መጡ፡፡ የመጡት እነዚህ ብዙ ሰዎች እያንዳንዱ አማኝ የየራሳቸውን ቋንቋ ሲናገር ሲሰሙ ተደነቁ፡፡ 7 እጅግ ተደንቀው እርስ በእርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፣ “እነዚህ ቋንቋችንን የሚናገሩ ሰዎች ሁሉ ከገሊላ የሚመጡ ናቸው፣ ስለዚህ እንዴት የእኛን ቋንቋዎች ሊያውቁ ቻሉ? 8 ሁላችንም አፍ የፈታንበትን የራሳችንን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን! 9 አንዳንዶቻችን ከጳርቴና ከሜድ ከኢላሜጤም አካባቢዎች የመጣን ነን፤ ሌሎቻችን ከመስጴጦምያ፣ ከይሁዳ ከቀጶዶቅያ፣ ከጳንጦስ እና እስያ የመጣን ነን፡፡ 10 ክፍርግያ እና ከጵንፍልያ፣ ከግብጽ፣ እና ከሊቢያ አካባቢዎች ከቀሬና ከተማ አቅራቢያ የመጡ አንዳንድ ሰዎችም አሉ፡፡ ከሮም ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት እዚህ የመጣን ሌሎቻችንም አለን፡፡ 11 የአይሁድ ተወላጆችና አይሁዳዊ ያልሆኑ እኛ አይሁዶች የምናምነውን የሚያምኑ በዚህ ይገኛሉ፡፡ ሌሎቻችን ከቀርጤስ ሰላጤና ከአረቢያ አካባቢ የመጣን ነን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር የሰራውን ታላላቅ ነገሮች በእኛ ቋንቋዎች የሚናገሩት እንዴት ነው? 12 ሰዎቹ በጣም ተደንቀውና እየሆነ ስለሚገኘውም ምን ማሰብ እንዳለባቸው አያውቁም ነበር፡፡ ስለዚህም እርስ በእርሳቸው እንዲህ እየተባባሉ ተጠያየቁ፣ “ይህ ምን ማለት ነው?” 13 አንዳንዶቹ ግን በሚያዩት አፌዙ፡፡ እንዲህም አሉ፣ “እነዚህ ሰዎች እንዲህ የሚናገሩት ያልፈላ ወይን ስለጠጡ ነው!” 14 14ስለዚህ ጴጥሮስ ከሌሎች አስራ አንድ ሐዋርያት ጋር ተነስቶ ቆሞ ለህዝቡ ጮህ ብሎ እንዲህ ብሎ ተናገረ፣ “እናንተ የይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም የምትገኙ ሁላችሁ፣ እኔን ስሙኝ፣ እየሆነ ያለውን እነግራችኋለሁ! 15 አንዳንዶቻችን እንደጠጣን አስባችኋል፣ ነገር ግን እኛ አልጠጣንም፡፡ ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ነው በዚህ የሚገኙ ሰዎች በዚህ ሰዓት ፈጽመው ጠጥተው አያውቁም! 16 ይልቁንም፣ በእኛ ላይ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል ከዘመናት አስቀድሞ የጻፈው አስደናቂ ነገር ነው፡፡ እርሱ እንዲህ ብሎ ጽፏል፡ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ 17 ‘በመጨረሻው ቀናት በየስፍራው ቅዱሱን መንፈሴን ለሁሉም እሰጣለሁ በውጤቱም፣ ወንዶች ልጆቻችሁ እና ሴቶች ልጆቻችሁ ከእኔ የሆነውን መልዕክት ለሰዎች ይናገራሉ፣ ከእናንተ መሀል ወጣቶች ከእኔ የሆነውን ራዕዮች ያያሉ፣ በመሀላችሁ የሚገኙ አዛውንቶች የምሰጣቸውን ህልሞች ያልማሉ፡፡ 18 በእነዚያ ቀናት ለአገልጋዮቼ ቅዱስ መንፈሴን እሰጣለሁ፣ ስለዚህም እነርሱ ከእኔ የሆነውን መልዕክት ለሰዎች መናገር ይችላሉ፡፡ 19 በሰማይ አስደናቂ ነገሮች እንዲሆኑ አደርጋሁ፣ አስፈላጊ ነገሮች እንደሚሆኑ ለማሳየት በምድር ላይ ተአምራቶችን አደርጋለሁ፡፡ እዚህ በምድር ላይ ደም፣ እሳትና ጭስ በየስፍራው ይሆናል፡፡ 20 በሰማይ ፀሀይ ጨለማ ሆና ለሰዎች ትታያለች፡፡ ጨረቃም ቀይ ትሆንባቸዋለች፡፡ እነዚያ ነገሮች እኔ፣ ጌታ እግዚአብሔር፣ በእያንዳንዱ ላይ ለመፍረድ ከመምጣቴ አስቀድሞ ይሆናሉ፡፡ 21 እንድረዳቸው የሚጠሩኝን ሁሉ እኔ አጽናናቸዋለሁ፡፡’” 22 ጴጥሮስ ንግግሩን ቀጠለ፣ “እስራኤላዊያን ወገኖቼ ሆይ እኔን ስሙኝ! የናዝሬቱ ኢየሱስ በመካላችሁ ሲኖር እርሱ ከእግዚአብሔር መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ አስደናቂ ተአምራቶችን እንዲያደርግ በማስቻል እርሱ እንደላከው እግዚአብሔር ለእናተ አረጋግጧል፡፡ ይህ እውነት መሆኑን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፡፡ 23 ምንም እንኳን ያንን ብታውቁም፣ ይህን ሰው ኢየሱስን ለጠላቶቹ አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፡፡ የሆነ ሆኖ፣ እግዚአብሔር ያን አስቀድሞ አቅዶት ነበር፣ እርሱም ስለዚያ ሁሉ ያውቅ ነበር፡፡ ከዚያ እናንተ የእግዚአብሔርን ህግ የማይታዘዙ ሰዎች ኢየሱስን እንዲገድሉ የግድ አላችሁ፡፡ እነርሱም እርሱን በመስቀል ላይ በምስማር በመስቀል ያን አደረጉ፡፡ 24 እርሱ ሞተ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር መልሶ አስነሳው፣ ምክንያቱም እርሱ ሞቶ መቅረት አይችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ኢየሱስ ዳግመኛ ሕያው እንዲሆን አደረገው፡፡” 25 “ከዘመናት አስቀድሞ ንጉስ ዳዊት መሲሁ የተናገረውን ጽፏል፣ ጌታ እግዚአብሔር፣ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ እኔ ያንን አውቃለሁ፡፡ አንተ በቀኜ ነህ፣ ስለዚህ ሊጎዱኝ የሚፈልጉትን አልፈራቸውም፡፡ 26 በዚህም ምክንያት ልቤ ደስ ይለዋል ሃሴትም አደርጋለሁ ደግሞም እንደምትረዳኝ አውቃለሁ፡፡ 27 ሙታን በሚኖሩበት ስፍራ እንድቆይ አታደርገኝም፡፡ አካሌን እንኳን እንዲበሰብስ አትተወዉም፣ ምክንያቱም እኔ ሁልጊዜ ለአንተ የተሰጠሁና ሁልጊዜም የምታዘዝህ ነኝ፡፡ 28 እንደገና እንዴት ሕያው እንደምሆን አሳይተኸኛል፡፡ አንተ እኔን በጣም ደስተኛ ታደርኛለህ ምክንያቱም አንተ ለዘለዓለም ከእኔ ጋር ነህ፡፡” 29 ጴጥሮስ ቀጠለ፣ “አይሁዳዊያን ወገኖቼ፣ አባታችን ንጉስ ዳዊት እንደሞተ እርግጠኛ ነኝ ደግሞም ሰዎች ቀብረውታል፡፡ በድኑ የተቀበረበት ስፍራ ዛሬም በዚህ ነው፡፡ 30 ንጉስ ዳዊት ነቢይ ነበር፣ እርሱ ከትውልዱ አንዱ ንጉስ እንደሚሆን እግዚአብሔር ቃል እንደገባለት ያውቅ ነበር፡፡ 31 ከዘመናት አስቀድሞ፣ እግዚአብሔር ምን እንደሚያደርግ ዳዊት ያውቅ ስለነበር መሲሁ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ዳግም ህያው እንደሚሆን ተናገረ፡፡ እግዚአብሔር መሲሁን ኢየሱስን ከሙታን ስፍራ እንደማይተወው፣ ወይም ሥጋው እንዲበሰብስ እንደማይፈቅድ ተናገረ፡፡” 32 “ይህ ሰው ኢየሱስ ከሞተ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደገና ህያው እንዲሆን አደረገ፡፡ እኛ ሁላችን፣ የእርሱ ተከታዮች የሆን፣ ይህን እናውቃለን ምክንያቱም እኛ እርሱን አይተናል፡፡ 33 እግዚአብሔር እርሱን በቀኙ በኩል በማስቀመጥ ከአባቱ ጋር እንዲገዛ በማድረግ ኢየሱስን እጅግ አከበረው፡፡ እርሱ መንፈስ ቅዱስን ለእኛ ሰጠን፣ ዛሬ እዚህ የምታዩትና የምትሰሙት ይህን ነው፡፡ 34 ዳዊት ስለራሱ እየተናገረ እንዳልነበረ እኛ እናውቃለን ምክንያቱም ዳዊት ኢየሱስ እንዳደረገው ወደ ሰማይ አላረገም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ዳዊት ራሱ ስለ መሲሁ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡ ጌታ እግዚአብሔር ለመሲሁ ጌታዬ እንዲህ ብሏል፣ 35 ‘ጠላቶችህን ሙሉ ለሙሉ እስከማሸነፍ እዚህ በቀኜ ግዛ’” 36 ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ንግግሩን አጠቃለለ፣ “ስለዚህ እናንተና መላው እስራኤላዊያን እናንተ በመስቀል ላይ የሰቀላችሁትንና የገደላችሁትን ይህንኑ ኢየሱስን ራሱን እግዚአብሔር ጌታና መሲህ እንዳደረገው እንድታውቁ እፈልጋለሁ፡፡” 37 ሰዎቹ ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት የተናገሩትን ሲሰሙ፣ ስህተት እንደሰሩ አወቁ፡፡ ሰዎች እንዲህ አሏቸው፣ ምን ማድረግ ይገባናል?” 38 ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፣ “እያንዳንዳችሁ ከኃጢአተኝነት ባህሪችሁ መመለስ አለባችሁ፡፡ አሁን በኢየሱስ ብታምኑ እኛ እናጠምቃችኋለን፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአታችሁን ይቅር ይላችኋል፣ ደግም ቅዱሱን መንፈሱን ይሰጣችኋል፡፡ 39 እግዚአብሔር ይህን ለእናንተና ለልጆቻችሁ ከዚህ ርቀው ለሚኖሩ ጭምር በኢየሱስ ለሚያምኑ ለሌሎች ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብቷል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር አምላካችን የእርሱ ህዝብ ለመሆን ለሚለምኑ ሁሉ ለእያንዳንዱ ቅዱሱን መንፈሱን ይሰጣል፡፡ 40 ጴጥሮስ ሌላም ብዙ ነገር በሀይል ተናገራቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፣ “ኢየሱስን የገፉትን ክፉ ሰዎችን በሚቀጣበት ጊዜ እናንተንም እንዳይቀጣ እንዲያድናችሁ እግዚአብሔርን ለምኑ!” 41 የጴጥሮስን መልዕክት የተቀበሉ ተጠመቁ፡፡ በዚያን ቀን ወደ አማኞች ህብረት የተቀላቀሉት ወደ ሶስት ሺህ ይጠጉ ነበር፡፡ 42 ሐዋርያት የሚያስተምሩትን ያለማቋረጥ ታዘዙ፡፡ ከሌሎች አማኞች ጋር ብዙ ጊዜ እየተገናኙ አብረው ይበሉና በየዕለቱም በጋራ ይጸልዩ ነበር፡፡ 43 ሐዋርያት ብዙ አይነት ተአምራታዊ ነገሮችን ያደርጉ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩ ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን በጣም ይፈሩና ያከብሩ ነበር፡፡ 44 በኢየሱስ ያመኑ ሁሉ ተመሳሳይ ነገር ያምኑና ዘወትር በአንድነት ይሰባሰቡ ነበር፡፡ ያላቸውንም ነገር ሁሉ እርስ በእርሳቸው ይከፋፈሉ ነበር፡፡ 45 ከጊዜ ወደ ጊዜ አንዳንዶቹ ከመሬታቸው እና ካላቸው ሌሎች ነገሮች እየሸጡ በመሀላቸው ላሉ ለሌሎች እንደሚያስፈልጋቸው ይሰጡ ነበር፡፡ 46 በየዕለቱ ምግባቸውን በደስታ እርስ በእርሳቸው ይከፋፈሉ፣ በቤቶቻቸው በአንድነት ይመገቡና የጌታን ዕራት እያከብሩ በየዕለቱ በመቅደስ አካባቢ ይገናኙ ነበር፡፡ 47 እንደዚህ እያደርጉ፣ እግዚአብሔርን ማመስገናቸውን ቀጠሉ፣ ደግሞም በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ አክብሯቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች በሚሆኑበት ጊዜ፣ በየዕለቱ ጌታ ኢየሱስ በኃጢአቶቻቸው የሚቀጡ ሰዎችን ከመንገዳቸው እየመለሰ የሚድኑ ሰዎችን ቁጥር ይጨምር ነበር፡፡