1 ከዚያም ሊቀ ካህኑ እስጢፋኖስን እንዲህ ብሎ ጠየቀው፣ “እነዚህ ሰዎች ስለ አንተ የሚናገሯቸው ነገሮች እውነት ናቸውን?” 2 እስጢፋኖስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “ወገኖቼ አይሁዶችና የተከበራችሁ ሽማግሌዎች፣ እባካችሁ አድምጡኝ! እኛ የምናመልከው የክብር አምላክ እግዚአብሔር ለአባታችን ለአብርሃም፣ ወደ ካራን ከተማ ከማምጣቱ አስቀድሞ ገና በመስጴጦምያ ሳለ ተገለጠለት፡፡ 3 እግዚአብሔር ለእርሱ እንዲህ አለው፣ ‘አንተና ቤተዘመዶችህ የምትኖርበትን ይህን ምድር ለቀህ ውጣና፣ እኔ ወደምመራህ ምድር ሂድ፡፡’ 4 ስለዚህም አብርሃም ክላውዲያ ተብሎም የሚታወቀውን ምድሩን ለቆ ወጣ፣ እናም በካራን ደርሶ በዚያ ኖረ፡፡ አባቱ ከሞተ በኋላ፣ እግዚአብሔር አሁን እናንተና እኔ ወደምንኖርበት ወደዚህ ምድር እንዲመጣ ነገረው፡፡ 5 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም በዚህ የራሱ የሆነ ምንም መሬት አልሰጠውም ነበር፣ ከዚህ ምድር ቁራሽ መሬት እንኳን አልሰጠውም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በኋላ ይህን ምድር ለእርሱና ለዘሩ እርስት አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት፡፡ ሆኖም በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ለሁልጊዜም የእርሱ አድርጎ የሰጠውን መሬት የሚወርስ ምንም ልጅ አልነበረውም፡፡ 6 በኋላ እግዚአብሔር ለአብርሃም እንዲህ ብሎ ነገረው፣ ‘ዘሮችህ ሄደው በባዕድ አገር ይኖራሉ፡፡ በዚያ ለአራት መቶ አመታት ይኖራሉ፣ እናም በእነዚያ ዘመናት መሪዎቻቸው ዘሮችህን ያጎሳቁላቸዋል፡፡ እንደ ባሪያ እንዲሰሩ ያስገድዷቸው፡፡ 7 ‘ነገር ግን እኔ እንደ ባሪያ እንዲሰሩ ያደረጓቸውን ሰዎች እቀጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ፣ የአንተ ዘሮች ያንን ምድር ለቀው ይወጣሉ፣ ወደዚህ ምድር መጥተው እኔን ያመልኩኛል፡፡’ 8 ከዚያ እግዚአብሔር፣ እያንዳንዱ በአብርሃም ቤት ያለ ወንድና ሁሉም ወንድ ዘሮቹ ሁላቸውም የእግዚአብሔር መሆናቸውን ለማሳየት መገረዝ እንዳለባቸው አዘዘ፡፡ በኋላ የአብርሃም ልጅ ይስሃቅ ተወለደ፣ ይስሃቅ ስምንት ቀን ሲሆነው አብርሃም እርሱን ገረዘው፡፡ በኋላ የይስሃቅ ልጅ ያዕቆብ ተወለደ፣ ያዕቆብ እኛ አይሁዶች አባቶች ወይም የቀደሙ አባቶቻችን ለምንላቸው አስራ ሁለት ወንዶች አባት ነበር፡፡ 9 የያዕቆብ ትልልቆቹ ልጆቹ ቅናተኛ እንደሆኑ ታውቃላችሁ ምክንያቱ አባታቸው ትንሹን ወንድማቸውን ዮሴፍን ይበልጥ ይወደው ስለነበረ ነው፡፡ ስለዚህም እርሱን ወደ ግብጽ ለወሰዱት ነጋዴዎች ሸጡት በዚያም ባሪያ ሆነ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዮሴፍን ረዳው፤ 10 ሰዎች እንዲሰቃይ ባደረጉት ጊዜ ሁሉ እርሱ ጠበቀው፡፡ እግዚአብሔር ዮሴፍ ጥበበኛ እንዲሆን አስቻለው፣ የግብፅ ንጉስ ፈርኦን ስለ ዮሴፍ በበጎ እንዲያስብ አደረገ፡፡ ስለዚህም በግብጽ ላይ እንዲገዛ በሀብቱ ላይ ሁሉ ፈርኦን ሾመው፡፡ 11 ዮሴፍ ያንን ስራ እየሰራ ሳለ፣ በግብፅና በከነዓን ጭምር የምግብ እጥረት የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ሰዎች ይሰቃዩ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ያዕቆብና የእርሱ ልጆችም በከነዓን ውስጥ በቂ ምግብ ማግኘት አልቻሉም፡፡ 12 ያዕቆብ ከግብፅ ሰዎች መግዛት የሚችሉት እህል እንዳለ ሲሰማ፣ የዮሴፍን ታላላቅ ወንድሞች እህል እንዲገዙ ወደዚያ ላካቸው፡፡ እነርሱ ሄደው ከዮሴፍ እህል ገዙ፣ ነገር ግን እርሱን አላወቁትም፡፡ ከዚያ ወደቤታቸው ተመለሱ፡፡ 13 የዮሴፍ ወንድሞች ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ግብፅ ሲሄዱ፣ እንደገና ከዮሴፍ እህል ገዙ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ እርሱ ማን እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም ፈርኦን የዮሴፍ ወገኖች ዕብራዊ እንደሆኑ አወቀ እንደዚሁም ደግሞ ከከነዓን የመጡት እነዚያ ሰዎች ወንድሞቹ እንደሆኑ አወቀ፡፡ 14 ከዚያ ዮሴፍ ወንድሞቹን መልሶ ወደቤታቸው ከላከ በኋላ ለአባታቸው ለያዕቆብ ዮሴፍ እርሱን እንደሚፈልገው ነገሩት እናም መላው ቤተሰቡ ወደ ግብፅ መጡ፡፡ በዚያን ጊዜ የያቆብ ቤተሰብ ሰባ አምስት ሰዎች ያህል ነበር፡፡ 15 ስለዚህም ያዕቆብ ያንን ሲሰማ፣ እርሱና መላው የእርሱ ቤተሰብ በግብፅ ለመኖር ሄዱ፡፡ ከዚያ በኋላ፣ ያዕቆብ በዚያ ሞተ፣ እናም ሌሎች አባቶችን፣ ልጆቹ ጭምር በዚያ ሞቱ፡፡ 16 አጽማቸው ወደ ምድራችን መጥቶ አብርሃም ከዔሞር ልጆች በገዛው መቃብር በሴኬም ከተማ ተቀበሩ፡፡ 17 እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል እንደገባት ከግብፅ ሊያወጣቸው ጊዜው በደረሰ ወቅት አባቶቻችን በጣም በዝተው ነበር፡፡ 18 ሌላ ንጉስ በግብፅ መግዛት ጀመረ፡፡ እርሱ ከመንገሱ ከረጅም ጊዜ አስቀድሞ ዮሴፍ የግብፅን ህዝብ በታላቅ ሁኔታ እንደረዳ አያውቅም ነበር፡፡ 19 ያ ንጉስ አባቶቻችንን በጭካኔ ሊያስወግድ ሞከረ፡፡ ተቃወማቸው ደግሞም እጅግ አሰቃያቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ አዳዲስ የሚወለዱ ህፃናቶቻቸውን እንዲሞቱ ከቤቶቻቸው እያወጡ እንዲጥሉ ትዕዛዝ ሰጣቸው፡፡ 20 በዚያን ወቅት ሙሴ ተወለደ፣ ህጻኑ በጣም ቆንጆ እንደሆነ እግዚአብሔር አየ፡፡ ስለዚህ ወላጆቹ ለሶስት ወራት በቤታቸው ውስጥ ደበቁት፡፡ 21 ከዚያ እርሱን ከቤት ማውጣት ነበረባቸው፣ ነገር ግን የፈርኦን ሴት ልጅ አገኘችውና እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ ተንከባከበችው፡፡ 22 ሙሴ በግብጽ ውስጥ ያለውን ትምህርት ሁሉ ተማረ፣ ሲያድግ በሀይል ይናገርና ይሰራ ነበር፡፡ 23 አንድ ቀን ሙሴ የአርባ አመት ሰው ሳለ፣ እስራኤላዊያን ወገኖቹን ሄዶ ለመጎብኘት ወሰነ፡፡ 24 አንድ ግብፃዊ አንዱን እስራኤላዊ ሲበድለው አየ፡፡ ስለዚህ እስራኤላዊውን ሰው ለመርዳት ተጠጋ፣ ግብፃዊውን በመግደል ለእስራኤላዊው ተበቀለ፡፡ 25 ሙሴ እስራኤላዊያን ወገኖቹ እነርሱን ከባርነት ነጻ ለማውጣት እግዚአብሔር እንደላከው የሚረዱ ይመስለው ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱ አይገባቸውም ነበር፡፡ 26 በማግስቱ፣ ሁለት እስራኤላውያን ወንዶች እርስ በእርሳቸው ሲደባደቡ አየ፡፡ እንዲህ በማለት ድብደባቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሞከረ፣ ‘ሰዎች እናንተ ሁለታችሁ እስራኤላውያን ወገኖች ናችሁ! ለምን እርስ በእርሳችሁ ትጎዳዳላችሁ?’ 27 ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኘው ሰው ሙሴን ገፈተረውና እንዲህ አለው፣ ‹ማንም አንተን በእኛ ላይ ገዥና ዳኛ አድርጎ አልሾመህም! 28 ትናንትና ግብጻዊውን እንደገደልከው እኔንም መግደል ትፈልጋለህ?’ 29 ሙሴን ይህን ሲሰማ ከግብፅ ወደ ምድያም ምድር ሸሸ፡ በዚያ ለጥቂት አመታት ኖረ፡፡ አገባ፣ እርሱና ሚስቱ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሯቸው፡፡ 30 አንድ ቀን ከአርባ አመታት በኋላ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንደ መልአክ ለሙሴ ተገለጠለት፡፡ በሲና ተራራ አጠገብ በሚገኝ በረሃ በሚነድ የእሳት ቁጥቋጦ መሀል እርሱ ተገለጠለት፡፡ 31 3ሙሴ ይህን ሲመለከት ተደንቆ ነበር፣ ምክንያቱም ቁጥቋጦው በእሳቱ አይበላም ነበር፡፡ ለመመልከት ይበልጥ ጠጋ ሲል፣ ጌታ ለእርሱ እንዲህ ሲል ሰማው፣ 32 ‘እኔ አባቶችህ ያመለኩኝ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ እኔ አብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ ያመለኩኝ እግዚአብሔር ነኝ፡፡’ ሙሴ መንቀጥቀጥ እስኪጀምር ድረስ በጣም ፈርቶ ነበር፡፡ ከዚያ በላይ ወደ ቁጥቋጦው ለማየት ፈርቶ ነበር፡፡ 33 ከዚያ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፣ ‘እኔን ማክበርህን ለማሳየት ጫማህን አውልቅ፡፡ ምክንያቱም እኔ በዚህ አለሁ፣ አንተ የቆምክበት ስፍራ በተለይ የእኔ ነው፡፡ 34 የግብፅ ሰዎች እንዴት ህዝቤን እጅግ እንደሚያስጨንቁ እኔ በእርግጥ አይቻለሁ፡፡ ከዚህ የተነሳ ህዝቤ በስቃይ ሲጮህ ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ ከግብፅ ነጻ ላወጣቸው ወርጃለሁ፡፡ አሁን ተዘጋጅ፣ ምክንያቱም መልሼ ወደ ግብፅ ልልክህ ነው፡፡’ 35 ይህ ሙሴ የእኛን የእስራኤል ሰዎችን ለመርዳት የሞከረ ነው፣ ነገር ግን እንዲህ በማለት አልተቀበሉትም፣ ‘ማንም ገዥና ዳኛ አድርጎ አልሾመህም!’ እግዚአብሔር ራሱ እንዲመራቸውና ከባርነት ነጻ እንዲያወጣቸው የላከው ሙሴን ነው፡፡ በቁጥቋጦው ውስጥ ያንን እንዲያደርግ መልአኩ ያዘዘው እርሱን ነው፡፡ 36 አባቶቻችንን ከግብጽ መርቶ ያወጣው ሙሴ ነው፡፡ እርሱ በቀይ ባህር፣ እና የእስራኤል ሰዎች በበረሃ በኖሩበት አርባ አመታት፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መሆኑን ለማሳየት ግብፅ ውስጥ ብዙ አይነት ተአምራቶችን አድርጓል፡፡ 37 ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ ያለው ይኸው ሙሴ ነው፣ ‘ከእናንተ ከራሳችሁ ሰዎች መካከል እንደ እኔ ያለ ነብይ ይኖራችሁ ዘንድ እግዚአብሔር ሌላ ሰው ያስነሳል፡፡’ 38 በበረሃ አብረው ከነበሩ እስራኤላዊያን መሀል የነበረው ይህ ሰው ሙሴ ነበር፤ እርሱ በሲና ተራራ ከእርሱ ጋር ከተነጋገረው መልአክ ጋር ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ የእኛን ህግጋት ለመልአኩ ሲሰጠው ሙሴ ነበር፣ መልአኩ የተናገረውን ለአባቶቻችን የነገረው ሙሴ ነበር፡፡ ለዘለዓለም እንዴት መኖር እንደሚቻል ከእግዚአብሔር ቃላትን የተቀበለውና እነዚያን ለእኛ ያስተላለፈው እርሱ ነበር፡፡ 39 የሆነ ሆኖ፣ አባቶቻችን ሙሴን መታዘዝ አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም፣ መሪያቸው እንዳይሆን ተቃወሙ፣ ደግሞም ወደ ግብፅ መመለስ ፈለጉ፡፡ 40 ስለዚህም ታላቅ ወንድሙን አሮንን እንዲህ አሉት፣ ‘የሚመሩንን አማልዕክት ለእኛ ጣኦቶችን ስራልን፡፡ ከግብጽ መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ የተባለ ሰው ምን እንደደረሰበት እኛ አናውቅም! 41 ስለዚህ ጥጃ የሚመስል መልክ ያለው ምስል ሰሩ፡፡ ከዚያ ያንን ጣኦት ለማክበር መስዋዕት አቀረቡለት፣ እነርሱ ራሳቸው ለሰሩት ዘፈኑ ጨፈሩ፡፡ 42 ስለዚህም እግዚአብሔር እነርሱን መመለሱን ተወ፡፡ ፀሀይን፣ ጨረቃንና በሰማይ ያሉ ከዋክብትን እንዲያመልኩ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ይህም ከነቢያት አንዱ እንዲህ ብሎ ከጻፈው ጋር ይስማማል፡ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘እናንተ የእስራኤል ሰዎች፣ በተደጋጋሚ እንስሳትን ስትገድሉና በበረሃ በነበራችሁባቸው በእነዚያ አርባ አመታት እንደ መስዋዕት ስታቀርቧቸው ለእኔ እያቀረባችኋቸው ነበራችሁን? 43 በተቃራኒው፣ የምታመልኩትን ሞሎክ የተባለውን አማልዕክት የሚወክል ጣኦት የያዘውን ድንኳናችሁን ተሸክማችሁ ከቦታ ቦታ ትሄዱ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሬምፉም የተባለውን ኮከብ ምስል ትሸከሙ ነበር፡፡ እነዚያ ጣኦታት እናንተ ያበጃችኋቸው ነበሩ፣ በእኔ ምትክ እነርሱን አመለካችሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ከቤታችሁ ርቃችሁ እንድትሰደዱ አደርጋለሁ ከባቢሎን አገር እንኳን ርቃችሁ እንድትሰደዱ አደርጋለሁ፡፡’ 44 “አባቶቻችን በበረሃ በነበሩ ጊዜ፣ በተቀደሰው ድንኳን እግዚአብሔርን አመለከቱ ይህም እርሱ በዚያ ከእነርሱ ጋር እንደ ነበረ ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ሙሴ እንዲሰራው ባዘዘው መልክ በትክክል አስመስለው ድንኳኒቱን ሰሩ፡፡ ድንኳኒቱም በተራራ ላይ በነበረ ጊዜ የተመለከተውን በትክክል ትመስል ነበር፡፡ 45 በኋላ፣ ሌሎች አባቶቻችን እያሱ ወደዚህ ምድር ሲመራቸው ያችን ድንኳን ይዘው ገቡ፡፡ ያ የሆነው እግዚአብሔር ቀድሞ እዚህ ይኖሩ የነበሩትን በሀይል አስወጥቶ ይህን መሬት የራሳቸው ባደረጉ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህም እስራኤላዊያን ይህን ምድር መውረስ ቻሉ፡፡ ድንኳኒቱ በዚህ ምድር ቆየች ንጉስ ዳዊት እስከገዛበት ጊዜ ድረስም በዚህ ነበረች፡፡ 46 ዳዊት እግዚአብሔርን ደስ አሰኘ፣ እግዚአብሔርንም እርሱና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቤት እንዲሰራ ጠየቀው፡፡ 47 ነገር ግን በምትኩ፣ የዳዊት ልጅ ሰለሞን ሰዎች እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቤት እንዲሰራ እግዚአብሔር ተናገረ፡፡” 48 “ሆኖም ግን፣ እግዚአብሔር ከሁሉም ነገር እንደሚበልጥ እናውቃለን፣ እርሱ ሰዎች በሰሩት ቤት ውስጥ አይኖርም፡፡ ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል እንደፃፈው ነው፡ 49 - 50 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ “ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድር የእግሬ ማሳረፊያ ናት፡፡ እኔ ራሴ በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ሰርቻለሁ፡፡ ስለዚህ እናንተ ሰብአዊ ፍጥረቶች እኔ ልኖር የምችልበትን ስፍራ መስራት አትችሉም!” 51 “እናንተ ሰዎች ለእርሱ ፍፁም ደንዳኖች ናችሁ! እናንተ ልክ እንደ አባቶቻችሁ ናችሁ! ልክ እነርሱ እንዳደረጉት እናንተም ሁልጊዜም መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ! 52 አባቶቻችሁ እያንዳንዱን ነቢይ አሰቃዩ፡፡ ሁልጊዜም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ያደረጉትን፣ ከረጅም ዘመን አስቀድሞ ክርስቶስ እንደሚመጣ የተናገሩትን ጭምር ገደሉ፡፡ ክርስቶስ መጣ! እርሱንም በቅርቡ ለጠላቶቹ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትና እንዲገድሉት ገፈፋችሁ! 53 እናንተ የእግዚአብሔርን ህግ የተቀበላችሁ ህዝቦች ናችሁ፡፡ እነዚያ ህጎች እግዚአብሔር ለአባቶቻችን መላእክት እንዲሰጧቸው ያደረጋቸው ናቸው፡፡ ሆኖም፣ እናንተ አልተዘዛችኋቸውም፡፡ 54 የአይሁድ መማክርት አባላትና በዚያ የነበሩ ሌሎችም እስጢፋኖስ የተናገረውን ሁሉ ሲሰሙ፣ በጣም ተቆጡ፡፡ በእርሱ በጣም ስለተቆጡ ጥርሳቸውን አፋጩ! 55 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠረው፡፡ ወደሰማይ ቀና ብሎ ሲመለከት ከእግዚአብሔር ዘንድ አብረቅራቂ ብርሃን አየ፣ እናም ኢየሱስን በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየው፡፡ 56 “እዩ፣” አለ፣ “ሰማይ ተከፍቶ አያለሁ፣ እናም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ!” 57 የአይሁድ መማክርት አባላትና ሌሎች ያን ሲሰሙ፣ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፡፡ እርሱን እንዳይሰሙ እጆቻቸውን በጆሯቸው ላይ አድርገው፣ ወዲያውኑ ወደ እርሱ ሮጡ፡፡ 58 ከኢየሩሳሌም ከተማ ጎትተው አውጥተዉት በድንጋይ ይወግሩት ጀመር፡፡ ይከሱት የነበሩ ሰዎች ድንጋይ በቀላሉ መወርወር እንዲችሉ የደረቡትን ልብስ አወለቁ፣ ልብሳቸውን ሳኦል የተባለ ወጣት እንዲጠብቅ በመሬት ላይ አስቀመጡ፡፡ 59 እስጢፋኖስ ድንጋይ እየወሩወሩበት እያለ እንዲህ ብሎ ጸለየ፣ “ጌታ ኢየሱስ፣ መንፈሴን ተቀበል!” 60 ከዚያ እስጢፋኖስ በጉልበቱ ወድቆ እንዲህ ሲል ጮኸ፣ “ጌታሆይ፣ ስለዚህ ኃጢአት አትቅጣቸው!” ይህን ከተናገረ በኋላ፣ ሞተ፡፡