ምዕራፍ 3

1 ነገር ግን ይህን እወቅ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት አደገኛ ዘመን ይመጣል፡፡ 2 ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትእቢተኞች፣ ትምክህተኞቸ፣ በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል የሚናገሩ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ 3 ተፈጥሮአዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ሰላምን የማይፈጥሩ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ አመጸኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ 4 ከዳተኞች፣ ምክርን የማይሰሙ፣ በትእቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፡፡ 5 እግዚአብሔርን የመምሰል መልክ አላቸው ነገር ግን ኃይሉን ይክዳሉ፣ ከእነዚህ ሰዎች ራቅ፡፡ 6 ከእነዚህም አንዳንዶች በቤተ ሰብ ውስጥ ሾልከው እየገቡ በኃጢአት የሚገረሙትንና በልዩ ልዩ ምኞትም የሚነዱትን ሞኞችን ሴቶች ይማርካሉ፡፡ 7 እነዚህ ሴቶች ሁል ጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ለመማር ይሞክራሉ፣ ነገር ግን ፈጽሞ ወደ እውነት እውቀት ሊደርሱ አይችሉም፡፡ 8 ኢያኔስ እና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደተቃወሙት፣ እነዚህ የስህተት አስተማሪዎች እውነትን ይቃወማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አዕምሮአቸው የተበላሸባቸው፣ የእምነታቸውም እውነተኝነት ያልተረጋገጠ ነው፡፡ 9 ዳሩ ግን የእነዚያ የሁለቱ ሰዎች ሞኝነት እንደተጋለጠ፣ እነዚህም ሞኝነታቸው ይገለጣልና አይሳካላቸውም፡፡ 10 አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ ዓላማዬን፣ እምነቴን፣ መጽናቴን፣ ፍቅሬን፣ ትእግስቴን፣ 11 ስደቴን፣ መከራዬን፣ በአንጾኪያ፣ በኢቆንዮን እና በልስጥራን የደረሰብኝን ሁሉ ተከትለሃል፡፡ ይህን ሁሉ ስደት በጽናት አልፌዋለሁ፣ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ፡፡ 12 በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሚወደው ሊኖሩ የሚፈልጉ ሁሉ ይሰደዳሉ፡፡ 13 ከፉ ሰዎች እና አታላዮች በክፋት እየባሱ ሌሎችንም እያሳቱና ራሳቸውም ችየሳቱ ይሄዳሉ፡፡ 14 አንተ ግን በተማርህበትና በምታምንበት ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደተማርከው ታውቃለህና፡፡ 15 ከሕፃንነትህ ጀምሮ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ስለሚገኘው መዳን ጥበብ ሊሰጡህ ስለሚችሉት ቅዱሳት መጻሕፍት አውቀሃል፡፡ 16 በእግዚአብሔር የተገለጡ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ለመሠረተ እምነት፣ በእምነትም ለመጽናት፣ በጽድቅም ላለው ምክር ይጠቅማሉ፣ 17 በመሆኑም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ የተዘጋጀ እና የታጠቀ እንዲሆን ያደርጉታል፡፡