ምዕራፍ 1

1 ከጳውሎስ፣ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉ ለተሰሎንቄ ሰዎች ቤተክርስቲያን። 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 3 ወንድሞች ሆይ፣ ስለ እናንተ ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ አለብን፣ ይህ ተገቢ ነውና፣ ምክንያቱም እምነታችሁ እጅግ እያደገ ነውና፣ የእያንዳንዳችሁ ፍቅርም ለሌሎች የሚተርፍ ሆኗል። 4 በመሆኑም በስደቶቻችሁና በመከራዎቻችሁ ሁሉ ስለ መጽናታችሁ ስለ ትዕግስታችሁና እምነታችሁ እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር አብያተክርስቲያናት መካከል በልበ ሙሉነት እንመሰክራለን። 5 እናንተ ደግሞ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት ብቁ ሆናችሁ ትቆጠሩ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ ጻድቅ የመሆኑ ግልጽ ምልክት ነው። 6 መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይመልስላቸው ዘንድ ይህ በእግዚብሔር ፊት ቅን ፍርድ ነው፣ 7 ጌታችን ኢየሱስ ከኀይሉ መላዕክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ከእኛ ጋር መከራን ለተቀበላችሁት ደግሞ እረፍትን ይሰጣችኋል። 8 እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ግን በሚነድ እሳት ይበቀላቸዋል። 9 ከጌታ ሀልዎትና ከኀይሉ ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት እየተቀጡ ይሰቃያሉ፣ 10 እርሱ በቅዱሳኑ ሊከበር በሚመጣበት በዚያን ቀን፣ ምስክርነታችንን አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ይገረምባቸዋል። 11 በዚህ ምክንያት እኛ ደግሞ አምላካችን ለጥሪአችሁ የተገባችሁ አድርጎ ይቆጥራችሁና መልካሙን ምኞታችሁንና ማናቸውንም የእምነት ሥራ በኀይል ይፈጽምላችሁ ዘንድ ባለማቋረጥ እንጸልይላችኋለን። 12 ይህም በአምላካችንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ምክንያት የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ እንዲከበርና እናንተም በእርሱ ትከብሩ ዘንድ ነው።