ምዕራፍ 1
1
ሳዖል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት በአማሌቃውያን ላይ ጥቃት ከማድረስ በመመለስ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቆየ፡፡
2
በሦስተኛው ቀን የተቀዳደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ፡፡ ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም ወደ መሬት ለጥ ብሎ ሰገደለት፡፡
3
ዳዊትም “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር አምልጬ የመጣሁ ነኝ” ሲል መለሰ፡፡
4
ዳዊትም፣ “እስቲ የሆነውን ሁሉ ንገረኝ” አለው፡፡ እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነት ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል ደግሞም ሞተዋል፤ ሳዖልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ፡፡
5
ዳዊትም ለወጣቱ፤ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
6
ወጣቱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት፤
7
ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም ‘እነሆኝ አለሁ’ አልኩት፡፡
8
እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፡፡ አኔም፣ ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት፡፡
9
እርሱም አለኝ ‘እኔ በታላቅ ስቃይ ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ፡፡
10
ስለሆነም፣ ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፤ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፣ ለጌታዬ አምጥቻለሁ፡፡” አለው፡፡
11
ከዚያም ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ፡፡
12
የወደቁት በሰይፍ ነበርና ለሳኦል ለልጁ ለዮናታንና ለእግዚአብሔር ሕዝብ አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾ፡፡
13
ዳዊትም ወጣቱን ሰውዬ፣ “የየት አገር ሰው ነህ?” ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም፣ “በአገሪቱ ውስጥ በመጻተኛነት የሚኖር አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ፡፡
14
ዳዊትም፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ንጉሥ በገዛ እጅህ ስትገድል ለምን አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው፡፡
15
ዳዊትም ከጎልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “ግደለው” አለው፤ ጎልማሳው ሰው ሄዶ መታው፣ አማሌቃዊውም ሞተ፡፡
16
ከዚያም ዳዊት ለሞተው አማሌቃዊ፣ “‘እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል አፍህ መስክሮብሃልና ደምህ በራስህ ላይ ነው” አለው፡፡
17
ከዚያም ዳዊት ለሳዖልና ለልጁ ለዮናታን የሚከተለውን የሐዘን እንጉርጉሮ አንጎራጎረ፡፡
18
እንዲሁም የቀስት እንጉርጉሮ የተባለውን ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ ይህም በያሸር መጽሐፍ ተጽፎአል፡፡
19
“እስራኤል ሆይ፣ ክብርህ ሞቶአል፣ በተራሮችህ ላይ ተገድሎአል! ኃያላኑ እንዴት ወደቁ!
20
የፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንዳይደሰቱ፣ ያልተገረዙት ሴት ልጆች ፌሽታ እንዳያደርጉ ይህን በጌት አትናገሩ፣ በአስቆሎናም መንገዶች አታውጁት፡፡
21
እናንት የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ ጠል አያረስርሳችሁ፣ ዝናብም አይውረድባችሁ፤ የቁርባን እህል የሚያበቅሉም እርሻዎች በዚያ አይኑሩ፤ በዚያ የኃያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፣ የሳዖል ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም፡፡
22
ከሞቱት ሰዎች ደም፣ ከኃያላኑም ገላ የዮናታን ቀስት ተመልሶ አልመጣም፤ የሳዖልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም፡፡
23
ሳዖልና ዮናታን በሕይወት እያሉ የሚዋደዱና ግርማ ያላቸው ነበሩ፤ ሲሞቱም አልተለያዩም፤ከንስርም ይልቅ ፈጣኖች ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ፡፡
24
እናንተ የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ፤ ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ ፤ ልብሶቻችሁንም በወርቀ-ዘቦ ላስጌጠላችሁ ለሳዖል አልቅሱለት፡፡
25
ኃያላን እንዴት እንዲህ በጦርነት መካከል ወደቁ! ዮናታን ከፍ ባሉ ስፍራዎቻችሁ ላይ ሞቶአል፡፡
26
ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤ አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበር፤ ከሴት ፍቅርም የላቀ ነበር፡፡
27
ኃያላን እንዴት ወደቁ፤ የጦር መሣሪዎቹስ እንዴት ከንቱ ሆኑ!”