1 በዳዊት የአገዛዝ ዘመንም በእስራኤል ውስጥ ለሦስት ዓመታት ረሃብ ተከስቶ ነበር፡፡ ዳዊትም ስለ ጉዳዩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም፡- “የረሃቡ ዘመን እንዲያበቃ፣ ሳኦል ብዙ የገባዖን ከተማ ሰዎችን ስለ ገደለ፣ የሳኦል ቤተ ሰብ መቀጣት አለበት” ብሎ መለሰለት፡፡ 2 የገባዖን ሰዎች በትውልድ እስራኤላውያን አልነበሩም፡፡ እነርሱ ከአሞር ሕዝብ ወገን ሲሆኑ፣እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር በወረሩ ጊዜ ከጥፋት ሊጠብቋቸው ልባዊ ቃል ኪዳን ገብተውላቸው የነበሩ አናሳ ቡድን ናቸው፡፡ ይሁንና ይሁዳና እስራኤል ብቸኛ የዚያ ምድር ኗሪዎች ሆነው እንዲቀሩ ለማስቻል በነበረው የጋለ ምኞት ሳኦል ዘራቸውን በሙሉ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር፡፡ ስለዚህ ንጉሡ የገባዖንን መሪዎች አስጠርቶ፡- 3 “ምን እንዳደርግላችሁ ትወዳላችሁ? እናንተ እኛን ለእግዚአብሔር የተሰጠነውንና ከእርሱም ስፍር- ቁጥር የሌላቸውን ነገሮች የተቀበልነውን ሕዝብ እንድትባርኩ፣ ሳኦል በሕዝባችሁ ላይ ያደረገውን ነገር እንዴት ማስተካከል እችላለሁ?” አላቸው፡፡ 4 እነርሱም ፡- “በእኛና በሳኦል ቤተ ሰብ መካከል ያለውን ጥል ብር ወይም ወርቅ በመስጠት ልታስተካክለው አትችልም፡፡ እኛም ከእስራኤላውያን ማንኛውንም ቢሆን የመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት፡፡ ስለዚህ ዳዊት፡- “ታዲያ አደርግላችሁ ዘንድ ምን ትጠይቁኛላችሁ?” ሲል ደግሞ ጠየቃቸው፡፡ 5 እነርሱም ሲመልሱለት፡- “ሳኦል እኛን ከምድረ-ገጽ ሊደመስሰን ፈልጎ ነበር፡፡ ከእኛ አንዳችንም በእስራኤል ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ለዘላለም ሊያጠፋን ወድዶ ነበር፡፡ 6 አሁንም ከሳኦል ትውልዶች መካከል ሰባት ሰዎችን በእጃችን አሳልፈህ ስጥ፡፡ እኛም በገባኦን ውስጥ፣ በከተማችን፣ እግዚአብሔር ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ሳኦል ይኖርባት በነበረችው ከተማ ውስጥ እግዚአብሔር በሚመለክበት ስፍራ እንሰቅላቸዋለን” አሉት፡፡ ንጉሡም፡- “በጣም ጥሩ፣እነርሱን አሳልፌ እሰጣችኋለሁ” አላቸው፡፡ 7 ንጉሡም እርሱና የሜምፊቦስቴ አባት ዮናታን እርስ በእርሳቸው በገቡት ልባዊ ቃል ኪዳን ምክንያት የሳኦል የልጁ ልጅ የሆነውን ሜምፊቦስቴን አሳልፎ አልሰጣቸውም፡፡ 8 ይልቁኑም ሄርሞንና ሜምፊቦስቴ ተብለው የሚጠሩትን የኢዮሄል ሴት ልጅና የሳኦል ጭማሪ ሚስት የሆነችው የሪጽፋ ሁለት ወንድ ልጆች፤ እንዲሁም የሳኦል ሴት ልጅ የነበረችውንና ባሏም ከሜሆላህ ከተማ የሆነ የቤርዜሊ ልጅ የኤስድሪኤል ሚስት የነበረችውን የሜሮብን አምስት ወንድ ልጆች ወሰደ፡፡ 9 ዳዊትም እነዚህን ሰዎች ለገባዖን ሕዝብ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም እነዚህን ሰባት ሰዎች ወደ ገባዖን ወስደው እግዚአብሔርን ያመልኩበት በነበረ አንድ ኮረብታ ላይ ሰቀሏቸው፡፡ እነርሱም የሞቱት ሕዝቡ የገብስ አዝመራውን መሰብሰብ በሚጀምርበት የዓመቱ ክፍለ ጊዜ ላይ ነበር፡፡ 10 ከዚያም ሪጽፋ ከፍየል ጸጉር የተሠራ ኮስኳሳ ልብስ ወስዳ አስከሬኖቹ በተኙበት ድንጋይ ላይ አነጠፈችው፡፡ እርሷም ሰዎቹ የገብሱን አዝመራ መሰብሰብ ከጀመሩበት ወቅት አንስታ የዝናቡ ወቅት እስኪጀምር ድረስ በዚያ ቆየች፡፡ እርሷም ቀን ቀን ማንኛውም ወፍ፣ ማታ ማታም ደግሞ ማንኛውም አውሬ አስከሬናቸውን እንዲነካ አልፈቀደችላቸውም፡፡ 11 አንድ ሰውም ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገረው፡፡ 12 ስለዚህ እርሱ ጥቂት አገልጋዮቹን ይዞ በገለዓድ አውራጃ ወደምትገኘው ወደ ኢያቢስ ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጽም አገኘ፡፡ የኢያቢስ ሕዝብ አጥንቶቻቸውን የፍልስጥኤም ሰዎች ሳኦልንና ዮናታንን ጊልቦዓ ተራራ ላይ በገደሉበት ቀን ሰቅለውት ከነበረበት ከቤትሳን ከተማ አደባባይ ሰርቀው ወስደው ነበር፡፡ 13 ዳዊትና ሰዎቹ የሳኦልንና የዮናታንን አጽም እንዲሁም በገባዖን ተሰቅለው የነበሩትን ሰባት ሰዎች አጽም ወሰዱ፡፡ 14 የዳዊት አገልጋዮችም በብንያም ነገድ ርስት ውስጥ በምትገኝ ዜላ ከተማ ውስጥ ወደ ነበረው ወደ ሳኦል አባት ወደ ቂስ መቃብር ሄዱ፡፡ እነርሱም የሳኦልንና የዮናታንን አጽም ደግሞ በዚያ ቀበሩ፡፡ እንደዚህም ንጉሡ እነርሱ ያደርጉት ዘንድ አዝዟቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ አከናወኑ፡፡ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ሳኦል በገባዖን የነበሩ ብዙ ሰዎችን በመግደሉ ምክንያት ዋጋው እንዲከፈል የሳኦል ቤተ ሰብ መቀጣቱን ተመልክቶ እስራኤላውያን ስለ ምድራቸው የጸለዩትን ጸሎት መልሶላቸው ረሃቡ እንዲያበቃ አደረገ፡፡ 15 የፍልስጥኤም ሠራዊት እንደገና የእስራኤልን ሠራዊት መዋጋት ጀመረ፡፡ ዳዊትና ወታደሮቹም እነርሱን ለመውጋት ሄዱ፡፡ ውጊያው ሲካሄድ ሳለ ዳዊት ደከመው፡፡ 16 ከፍልስጥኤማውያን ሰዎች አንዱ ዳዊትን ልገድለው እችላለሁ ብሎ አሰበ፡፡ ስሙም ይሽቢብኖብ ነበር፡፡ እርሱም ግዙፎች የሆኑ ሰዎች ትውልድ ወገን ነበር፡፡ ክብደቱ ሦስት ተኩል ኪሎ ግራም የሚመዝን የናስ ጦር ተሸክሞ አንድ አዲስ ሠይፍም ይዞ ነበር፡፡ 17 አቢሣ ግን ዳዊትን ሊያግዘው መጣ፣ ግዙፉንም ሰው አጥቅቶ ገደለው፡፡ ከዚያም የዳዊት ወታደሮች ከዚህ በኋላ ከእነርሱ ጋር እንደገና ወደ ጦርነት ላለመሄድ ቃል እንዲገባ ግድ አሉት፡፡ እነርሱም፡- “አንተ ብትሞትና ከትውልድህ ንጉሥ የሚሆን አንድም ሰው ባይገኝ፣ ያ በእስራኤል ውስጥ የመጨረሻውን ብርሃን እንደ ማጥፋት ይሆናል” አሉት፡፡ 18 ይህ ከተፈጸመ ጥቂት ጊዜ በኋላ ጎብ በሚባለው መንደር አቅራቢያ ከፍልስጥኤም ሠራዊት ጋር ጦርነት ተካሄደ፡፡ በውጊያውም ወቅት ከኩሳ ጎሣ የሆነው ሴቦካይ ከራፋይም ግዙፍ ሰዎች ትውልድ መካከል አንዱ የሆነውን ሳፍን ገደለው፡፡ 19 ጥቂት ጊዜ እንዳለፈም ጎብ በሚባለው ስፍራ ላይ ከፍልስጥኤም ሠራዊት ጋር ሌላ ጦርነት ተካሄደ፡፡ ውጊያው እየተካሄደ ሳለ ከቤተልሄም የሆነው የያሪ ወንድ ልጅ ኤልያናን የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ በጣም ወፍራም የሆነውን የጌቱን ሰው የጎልያድን ወንድም ገደለው፡፡ 20 ቆይቶም ሌላ ጦርነት በጌት አቅራቢያ ተደረገ፡፡ በዚያም ጦር ግንባር ውስጥ መዋጋት ደስታ የሚፈጥርለት አንድ ግዙፍ ሰው ነበር፡፡ እርሱም በእያንዳንዱ እጁ ላይ ስድስት ጣቶች በእያንዳንዱ እግሩ ላይም ስድስት ጣቶች ነበሩት፡፡ ራፋይም ከሚባሉት ግዙፍ ሰዎች ዝርያ የመጣ ነበር፡፡ 21 ዳሩ ግን እርሱ በእስራኤላውያን ሠራዊት ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ሲሳደብ የዳዊት ታላቅ ወንድም የሣማ ወንድ ልጅ ዮናታን ገደለው፡፡ 22 እነዚያ አራት ሰዎች በዳዊትና በወታደሮቹ የተገደሉ በጌት ይኖሩ የነበሩ ከራፋይም ግዙፍ ዝርያ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡