ምዕራፍ 1
1
ክርስቶስ አገልጋይና ሐዋርያ ከሆነው ስምዖን ጴጥሮስ፤ በአምላካችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ አማካይነት የተቀበልነውን ዐይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉት፤
2
እግዚአብሔርንና ጌታችንን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
3
በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እግዚአብሔርን በማወቅ እንድንኖር ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገን ሁሉ በመለኮቱ ኀይል ተሰጥቶናል።
4
በእነዚህ ነገሮች አማካይነት እጅግ የከበረና ታላቅ ተስፋ ሰጠን፤ ይህንም ያደረገው በክፉ ምኞቶች ሰበብ በዓለም ካለው ምግባረ ብልሹ ሕይወት አምልጣችሁ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ ነው።
5
በዚህም ምክንያት፣ የሚከተሉትን ነገሮች ለመጨመር ትጉ፣
በእምነታችሁ ላይ ደግነትን፣ በደግነት ላይ ዕውቀትን፣
6
በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እግዚአብሔርን መምሰልን፤
7
እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ ላይ ወንድማዊ መዋደድን፣ በወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
8
እነዚህ ነገሮች በውስጣችሁ ቢኖሩና በውስጣችሁ ቢያድጉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ዳተኞችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋል።
9
እነዚህ ነገሮች የሌሉት ግን ዕውር ነው፤ በቅርብ ያለውን ብቻ ያያል፤ ከቀድሞው ኀጢአቱ መንጻቱንም ረስቶአል።
10
ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ለማጽናት ትጉ፤ ይህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉም፤
11
በዚህም ወደ ጌታችንና አዳኛችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋል።
12
ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ዘወትር እናንተን ከማሳሰብ ቸል አልልም።
13
በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ማሳሰብ ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፤
14
ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ለቅቄ እንደምሄድ ዐውቃለሁ፤
15
ከተለየኋችሁም በኋላ እነዚህን ነገሮች ዘወትር እንድታስቡ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።
16
ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኀይልና ስለ ዳግም መምጣቱም በነገርናችሁ ጊዜ ግርማውን በዐይናችን አይተን መሰከርን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም።
17
«በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው» የሚል ድምፅ ከግርማዊው ክብር በመጣለት ጊዜ፣ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ሞገስን ተቀብሎአል።
18
ከእርሱ ጋር በተቀደሰው ተራራ ላይ በነበርንበት ጊዜ ይህን ከሰማይ የመጣውን ድምፅ ሰምተነዋል።
19
ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋ ድረስ በጨለማ ስፍራ ለሚያበራ መብራት እንደምትጠንቀቁ፣ የንጋቱ ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ።
20
ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት የሚገኘውን የትንቢት ቃል ማንም ሰው በራሱ መንገድ የሚተረጒመው አይደለም፤
21
ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም።