1 የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡ 2 ሕዝቅያስም ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፡፡ እርሱም በኢያሩሳሌም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም አቢያ የምትባል የዘካርያስ ልጅ ነበረች፡፡ 3 ሕዝቅያስም የአባቱን የንጉሥ ዳዊትን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡ 4 የአሕዛብን የማምለክያ ስፍራዎች አስወገደ፤ የድንጋይ ዐምዶችንም ሰባብሮ አጠፋ፤ ኣሼራ ተብላ በምትጠራው ሴት አምላክ ስም የተቀረጹትን ምስሎች ሁሉ አፈረሰ፡፡ ሙሴ ከነሐስ ሠርቶት የነበረውን ኔሑሽታን ተብሎ የሚጠራውን የእባብ ምስል ሰባብሮ አደቀቀ፤ ምክንያቱም እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን ለእርሱ ዕጣን ያጥኑለት ነበር፡፡ 5 ሕዝቅያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ተማመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ ወዲህ እርሱን የመሰለ ሌላ ንጉሥ በይሁዳ አልተነሣም፡፡ 6 ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ ከእግዚአብሔር መንገድ የራቀበት ጊዜ የለም፤ ለሙሴ የሰጣቸውን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽም ነበር፡፡ 7 ስለዚህም እግዚአብሔር ከሕዝቅያስ ጋር ስለነበረ የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር፡፡ ሕዝቅያስም በአሦር ንጉሠ ነገሥት ላይ ዐምፆ ለእርሱ መገዛትን አሻፈረኝ አለ፡፡ 8 ፍልስጥኤማውያንንም ድል ነሥቶ ከትንሽ እስከ ታላቅ የተመሸጉ ከተማ ጋዛንና በዙሪያው የሚገኘውን ግዛት፣ የሚኖሩበትን ስፍራ ሁሉ አጠቃ፡፡ 9 ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት ማለትም የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር በእስራኤል ላይ አደጋ በመጣል ሰማርያን ከበበ፡፡ 10 በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ሰማርያ በሙሉ ተያዘች፤ ይህም የሆነው ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት ሆሴዕም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር፡፡ 11 የአሦር ንጉሠ ነገሥት እስራኤላውያንን ማርኮ ወደ አሦር በመውሰድ ከእነርሱ ጥቂቶቹን በአላሔ ከተማ፣ ጥቂቶቹን በጋዛ አውረጃ በሚገኘው በአቦር ወንዝ አጠገብ፣ ሌሎቹን ደግሞ በሜዶን ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፡፡ 12 ይህም የሆነበት ምክንያት እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ነበር፤ ይኸውም እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፈረሱ፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ አማካይነት ለተሰጠ ሕግ ሁሉ ታዛዦች ሆነው አልተገኙም፤ ለመስማትም ሆነ ሕጉን ለመጠበቅ አሻፈረን አሉ፡፡ 13 ከዚያም ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሠ ነገሥት ሰናክሬም አደጋ በመጣል የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ያዘ፡፡ 14 ስለዚህም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በለኪሶ ሰፍሮ ለነበረው ለሰናክሬም፣ እኔ በድያለሁ፤ እባክህን እኔን ተወኝ፤ የምትጠይቀኝን ሁሉ እልክልሃለሁ ሲል መልእክት ላከ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ለይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እኔ የምፈልገው ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንድትልክልኝ ነው ሲል መለሰለት፡፡ 15 ስለዚህም ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥተ ዕቃ ግምጃ ቤት የነበረውን ብር ሁሉ ሰብስቦ ላከለት፡፡ 16 እንዲሁም በእግዚዚብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በሮች ላይ ተለብጦ የነበረውን ወርቅና እርሱም ራሱ በቤተ መቅደሱ የበር ዐምዶች ላይ ለብጦት የነበረውን ወርቅ ጭምር ወደ ሰናክሬም ላከ፡፡ 17 ነገር ግን የአሦር ንጉሠ ነገሥት እንደገና የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት ከለኪሶ ተንቀሳቅሶ ወደ ኢየሩሳሌም በመዝመት በሕዝቅያስ ላይ አደጋ እንዲጥልበት አዘዘ፤ ሠራዊቱም ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ሦስት የጦር አዛዦቹ የሚመራ ነበር፡፡ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ደረሱ ከላይኛው ኩሬ ውሃ በሚተላለፍበት ቦይ አጠገብ ወደ ልብስ አጣቢዎች መስክ የሚወስደውን መንገድ ያዙ፡፡ 18 ከዚያ ወደ ሕዝቅያስ መልእክት ላኩበት፤ ሕዝቅያስም አገልጋዮቹ የሆኑ ሦስት ባለሥልጣኖች ሄደው እንዲገናኙአቸው አዘዘ፡፡ እነርሱም የቤተ መንግሥቱ ኃላፊ የሆነው የኬልቂያስ ልጅ ኤልያቄም፣ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ የሆነው ሳምናስና የቤተ መዛግብት ኃላፊ የሆነው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ነበሩ። 19 ስለዚህም የአሦር ዋና የጦር አዛዥ እንዲህ አላቸው፡- ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፣ ‘ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፡- እንደዚህ የተማመንክበት ነገር ምንድን ነው? 20 በጦርነት የሚረዳ ኃይል እንዳለህ የተናገርከው ከንቱ ቃላት ናቸው፤ በእኔ ላይ ለማመጽ የቻልከው በምን ተማምነህ ነው? 21 የግብጽ ንጉሥ ይረዳኛል ብለህ አስበህ ከሆነ የተቀጠቀጠ ሸምበቆ እንደሚመረኮዝ ሰው መሆንህ ነው፤ እርሱ ተሰብሮ ስንጣሪው እጅህን ያቆስልሃል፤ እንግዲህ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚተማመኑበት ሁሉ እንዲህ ነው’ ሲል ተናገረ፡፡ 22 የአሦር የጦር አዛዥ ንግግሩን በመቀጠል እንደገና እንዲህ አለ፡- አምላክህ እግዚአብሔር እንደሚረዳህ ታስብ እንደሆነ፣ ይህ እንዳይሆን አንተ የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ደምስሰህ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ማምለክ የሚገባቸው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው በአንድ መሠዊያ ብቻ ነው ብለህ ወስነሃል፡፡ 23 አሁንም በንጉሠ ነገሥቱ ስም ለፍልሚያ እጠይቅሃለሁ፤ መጋለብ የሚችሉ በቂ ሰዎች ታገኝ አንደ ሆነ እስቲ ሁለት ሺህ ፈረሶች ልስጥህ፡፡ 24 አንተ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ከሆነው ከአሦር ተራ የጦር መኮንን ጋር እንኳ መወዳደር አትችልም፤ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይልኩልኛል ብለህ የምትጠባበቀውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ 25 እኔ በአንተ አገር ላይ አደጋ የጣልኩባትና የደመሰስኳት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዞኛል፡፡ 26 ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ ይህን የጦር አዛዥ ትርጉሙን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጥር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን አሉት፡፡ 27 የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣቸሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? እንደ እናንተ ኩሳቸውን ለመብላትና ሽንታቸውን ለመጠጣት ለሚገደዱ ሰዎችም ጭምር ስለ ሆነ እኔ የምናገረውን በቅጥር ላይ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲሰሙት እንድናገር አልላከኝምን? ሲል መለሰላቸው፡፡ 28 ከዚያም የአሦር የጦር አዛዥ ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ ጮኸ፡- የአሦር ንጉሠ ነገሥት የሚነግራችሁን ስሙ፤ 29 በሕዝቅያስ አትታለሉ፤ እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም፡፡ 30 ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ ያድናችኋል፤ ከተማችንም በአሦርያውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል እያለ የሚሰብካችሁን አትስሙት፡፡ 31 ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት ከከተማችሁ ወጥታችሁ እጃችሁን እንድትሰጡ አዞአችኋል፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁም እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላና የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጉድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፡፡ 32 ይህም ሁሉ የሚሆነው ንጉሠ ነገሥቱ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር ወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ምድሪቱም የወይራ ፍሬና የወይራ ዘይት እንዲሁም ማር የሞላባት ናት። ንጉሠ ነገሥቱ የሚያዛችሁን ብትፈጽሙ በሕይወት ትኖራላችሁ እንጂ አትሞቱም፡፡ ስለዚህ ሕዝቅያስ፣ “እግዚአብሔር ይታደጋችኋል” እያለ በመስበክ አያሙኛችሁ፡፡ 33 ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት አንዱ እንኳ ከአሦር ንጉሠ ነገሥት እጅ አገሩን ያዳነ ይገኛልን? 34 ታዲያ ይህ ከሆነ የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሴፈርዋይ፣ የሄናና የዒዋ አማልክትስ የት ደረሱ? ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ማዳን ችሎአልን? 35 የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ንጉሠ ነገሥቶቻቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እንግዲህ እናንተ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው? 36 ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ፡፡ 37 ከዚያም ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቀርበው የአሦራውያን የጦር አዛዥ የተናገረውን አስረዱት፡፡