ምዕራፍ 12

1 ኢዩ በእስራኤል በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ኢዮአስ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፡፡ እርሱም በኢየሩሳሌም አርባ ዓመት ገዛ፡፡ እናቱም ሳብያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች፡፡ 2 ካህኑም ዮዳሄ ይመክረውና ያስተምረው ስለ ነበር፣ ኢዮአስ በዕድሜው ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፡፡ 3 ነገር ግን በየኮረብታዎቹ ላይ የሚገኙት የአሕዛብ ማምለኪያዎች ስላልተደመሰሱ ሕዝቡ በዚያ ዕጣን እያጠኑ መሥዋዕት ማቅረባቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፡፡ 4 ኢዮአስም ካህናትን ጠርቶ በቤተ መቅደስ ከሚቀርበው መሥዋዕት ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ መባ ሆኖ የሚገባውን ገንዘብ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አዘዘ፤ ይኸውም ቋሚ ከሆነው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር መባ ሆኖ የሚቀርበውንና በበጎ ፈቃድ ሕዝቡ የሚያመጣውን ስጦታ ሁሉ የሚያጠቃልል ነበር፡፡ 5 እያንዳንዱ ካህን ከሚያገለግላቸው ሰዎች የሚገኘውን የገንዘብ መባ ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ገንዘቡንም እንዳስፈላጊነቱ ለቤተ መቅደሱ ጥገና አገልግሎት እንዲያውሉት ነገራቸው፡፡ 6 ነገር ግን ኢዮአስ እስከ ነገሠበት እስከ ሃያ ሦስተኛው ዓመት ድረስ ካህናቱ በቤተ መቅደሱ ላይ ምንም ዓይነት እድሳት አላደረጉም፡፡ 7 ስለዚህም ኢዮአስ ዮዳሄንና ሌሎቹንም ካህናት ወደ እርሱ ጠርቶ ቤተ መቅደሱን ያላደሳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? ከዛሬ ጀምሮ የምትቀበሉትን ገንዘብ መያዝ የለባችሁም፤ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ይውል ዘንድ ገንዘቡን አስረክቡ አላቸው፡፡ 8 ካናቱም በዚህ ተስማምተው ቤተ መቅደሱን በራሳቸው ለማደስ የነበራቸውን ተግባር አቆሙ፡፡ 9 በዚህ ፈንታ ዮዳሄ አንድ ሣጥን ወስዶ በመክደኛው ላይ ቀዳዳ አበጀ፤ ሣጥኑንም ወስዶ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ በስተ ቀኝ በሚገኘው መሠዊያ አጠገብ አኖረው፤ የየዕለቱ ተረኞች የነበሩትም ካህናት ለአምልኮ የሚመጡት ሰዎች የሚሰጡትን የገንዘብ መባ እየተቀበሉ በሣጥኑ ውስጥ ያስገቡት ነበር፡፡ 10 ሣጥኑም በሚሞላበት ጊዜ የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና ሊቀ ካህናቱ እየመጡ ገንዘቡን በመቁጠር በከረጢት እያሰሩ ያኖሩት ነበር፡፡ 11 ትክክለኛውን ሒሳብ አጣርተው ከመዘገቡ በኋላ ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ ኃላፊዎች ያስረክቡ ነበር፤ እነርሱም ገንዘቡን ተረክበው ለአናጢዎችና ለግንበኞች ይሰጡ ነበር፡፡ 12 ለድንጋይ ጠራቢዎች፣ ለማደሻ አገልግሎት የሚውል እንጨትና ድንጋይ ለሚገዙና እንዲሁም ለልዩ ልዩ አስፈላጊ ነገሮች ለሚውል ተግባር ሁሉ ይከፍሉ ነበር፡፡ 13 ነገር ግን ከብር ለሚሠሩ ጎድጓዳ ሳሕኖች የዐመድ ማጠራቀሚያ ጎድጓዳ ወጭት፣፣ እምቢልታ ወይም ደግሞ ከብርና ከወርቅ ለሚሠሩ ንዋያተ ቅዱሳት ከዚያ ገንዘብ ላይ ተነሥቶ የሚከፈል ሒሳብ አልነበረም፡፡ 14 ያ ገንዘብ በሙሉ በቤተ መቅደሱ እድሳት ተግባር ላይ ለተሰማሩት ሠራተኞች ብቻ የሚውል ነበር፡፡ 15 ለሥራው ኃላፊነት የተመረጡትም ሰዎች ፍጹም ታማኞች ስለ ነበሩ ገንዘቡን የሰጡአቸው ሰዎች አይቆጣጠሩአቸውም ነበር፡፡ 16 ስለ በደልና ስለ ኃጢአት መሥዋዕት የሚከፈለው ገንዘብ ግን ለካህናቱ ጥቅም የሚውል እንጂ ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ አይገባም ነበር፡፡ 17 በዚያ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ አዛሄል በጌት ከተማ ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ ቀጥሎም በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ተመለሰ፡፡ 18 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስም ከእርሱ በፊት የነበሩትን ነገሥታት ማለትም ኢዮሳፍ፣ ኢዮራምና አካዝያስ ለእግዚአብሔር ለይተው ያኖሩትን መባና የራሱን መባ ጨምሮ በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ግምጃ ቤቶች የነበረውን ወርቅ ሁሉ በመሰብሰብ ገጸ በረከት አድርጎ ለንጉሥ አዛሄል ላከለት፡፡ ሐዛሄልም ይህን ተቀብሎ ሠራዊቱን ከኢየሩሳሌም መለሰ፡፡ 19 ንጉሥ ኢዮአስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን? 20 ከዚህ በኋላ የንጉሥ ኢዮአስ ባለሥልጣኖች አንድ ላይ ተነሥተው አድመውበት ወደ ሲላ ሲሄድ በሚሎ ጥቃት አደረሱበት፡፡ 21 የሰምዓት ልጅ ዮዛካርና የሾሜር ልጅ ዮዛባት ኢዮአስን ገደሉት፡፡ በዳዊት ከተማ በሚገኘው የነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም ፈንታ ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ፡፡