ምዕራፍ 1

1 አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞአብ በአስራኤል ላይ ዐመፀ፡፡ 2 በዚያን ጊዜ የአስራኤል ንጉሥ አካዝያስ በሰማርያ ቤተ መንግሥቱ ሳለ ከሰገነቱ ላይ ወድቆ ክፉኛ ቆስሎ ነበር፤ እርሱም እኔ ከዚህ ሕመም እድን እንደሆነ በፍልስጥኤም የአቃሮን ከተማ አምላክ የሆነውን ብዔልዜቡል ጠይቁልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ላከ፡፡ 3 ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔሌዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ ነውን? 4 ስለዚህ እግዚአብሔር እነሆ አንተ ትሞታለህ እንጂ አትፈወስም፤ ከተኛህበት አልጋም አትነሣም፤ ብሎሃል በሉት፡፡ ከዚያም ኤልያስ ትቶ ሄደ፡፡ 5 መልእተኞቹም ወደ ንጉሡ ተመልሰው ሄዱ፤ ንጉሡም ስለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ? ሲል ጠየቃቸው፡፡ 6 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ አንድ ሰው በመንገድ አግኝቶን ወደ አንተ ተመልሰን እንድንመጣና እግዚአብሔር ስለ አንተ የተናገረውን እንድናስረዳህ አዘዘን፤ እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክህበት ምክንያት ምንድን ነው? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከዚህ ሕመም አትፈወስም፤ ከተኛህበትም አልጋ አትነሣም! 7 ንጉሡም በመንገድ ያገኛችሁት ይህንን ቃል የነገራችሁ ያ ሰው እንዴት ያለ ነው? ሲል ጠየቃቸው፡፡ 8 እነርሱም ጠጉራም ልብስ ለብሶ በወገቡ ዙሪያ የጠፍር ቀበቶ የታጠቀ ነው ሲሉ መለሱለት፡፡ ንጉሡም እርሱማ ኤልያስ ነው! አለ፡፡ 9 ከዚህም በኋላ ንጉሡ አንዱን የጦር መኮንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሄዶ ኤልያስን ይዞ ያመጣለት ዘንድ አዘዘው፡፡ መኮንኑም ኤልያስን በአንድ ኮረብታ ላይ ተቀምጦ አገኘውና የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል አለው፡፡ 10 ኤልያስም እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ አለው፤ ወዲያውኑ እሳት ከሰማይ ወርዶ መኮንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ፡፡ 11 ንጉሡም እንደገና ሌላውን መኮንን ከኀምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ እርሱም ወደ ኤልያስ ወጥቶ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ አሁኑኑ ወርደህ ወደ እርሱ እንድትመጣ ንጉሡ አዞሃል አለው፡፡ 12 ኤልያስም እኔስ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንኩ እሳት ከሰማይ ወርዶ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ይብላ አለው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር እሳት መኮንኑንና ኀምሳዎቹን ሰዎች በላ፡፡ 13 ንጉሡም ለሦስተኛ ጊዜ ከኀምሳ ሰዎች ጋር ሌላ መኮንን ላከ፤ ይህኛው መኮንን ግን ወደ ኮረብታው በመውጣት በኤልያስ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት ሰዎች ምሕረት አድርግልን፤ ሕይወትችንንም ከሞት አድን፣ 14 ሌሎቹን ሁለት መኮንኖችና ተከታዮቻቸውን ሁሉ ከሰማይ የወረደ እሳት በልቶአቸዋል፤ ለእኔ ግን እባክህ ምሕረት አድርግልኝ፡፡ 15 የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን ከእርሱ ጋር አብረህ ውረድ፤ ከቶም አትፍራ አለው፡፡ ስለዚህም ኤልያስ ከመኮንኑ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ፡፡ 16 እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን እንዲጠይቁ መልእክተኞችን የላክህ በእስራኤል አምላክ እንደሌለ በመቁጠርህ ነውን? ስለዚህ ከተኛህበት አልጋ ሳትወርድ ትሞታለህ እንጂ አትድንም አለው፡፡ 17 ስለዚህ እግዚአብሔር በኤልያስ አማካይነት በተናገረው ቃል መሠረት አካዝያስ ሞተ፡፡ አካዝያስ ወንዶች ልጆች ስላልነበሩት በእርሱ ፈንታ ተተክቶ ወንድሙ ኢዮራም ነገሠ። ይህም የሆነው የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ነበር፡፡ 18 ንጉሥ አካዝያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኝ የለምን?