ምዕራፍ 1

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ እና ወንድማችን ከሆነው ጢሞቲዎስ፥ በቆሮንቶስ ለምትገኝ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን እንዲሁም በመላው አካይያ ላሉ አማኞች ሁሉ፡ 2 ከእግዚአብሔር ከአባታችን እንዲሁም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋና ሰላም ለናንተ ይሁን። 3 የምህረት አባት፥ የመፅናናት አምላክ እና በመከራችን ሁሉ የሚያፅናናን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። 4 እግዚአብሔር በመከራችን ሁሉ ያፅናናል፥እኛም ራሳችን በእርሱ በእግዚአብሔር በተፅናናንበት መፅናናት ልክ ሌሎችን ማፅናናት እንችላለን። 5 ምክንያቱም የክርስቶስ መከራ በእኛ ላይ እንደበዛ፥ መፅናናታችንም በክርስቶስ በኩል እንዲሁ ይበዛልናል። 6 ነገር ግን መከራን ብንቀበል፥ስለናንተ መፅናናት እና ድነት ነው። ወይንም ደግሞ የእኛ መፅናናት የእናንተም መፅናናት ማለት ነው፤ይህም እኛ በምንቀበለው መከራ እናንተም በተመሳሳይ መልኩ በትእግስት አብራችሁን ስለምትካፈሉ ነው። 7 በናንተም ያለን መታመን ፅኑ ነው፥በመከራችን እንደምትካፈሉ ሁሉ በመፅናናታችንን ደግሞ እንደምትካፈሉ እናውቃለን። 8 ወንድሞች ሆይ፥በእስያ ስለደረሰብን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ በህይወት ለመኖር ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከአቅማችን በላይ ከብዶን ነበር። 9 በርግጥም ሞት ተፈርዶብን ነበር። ሆኖም ግን ያ የደረሰብን መከራ ሙታንን በሚያስነሳ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን አደረገን። 10 ከብርቱ ጥፋት አዳነን እንዲሁም ያድነናል። መታመናችንን በእርሱ ላይ አድርገናል፤እርሱም ይታደገናል። 11 በእናንተም የፀሎት ድጋፍ አምላካችን ስራውን ይሰራል። በመቀጠልም በብዙዎች ፀሎት አማካኝነት ለእኛ ስለተሰጠው ሞገስ በርካቶች ምስጋናን ያቀርባሉ። 12 የምንመካው በህሊናችን ምስክርነት ላይ ነው። ምክንያቱም በዚህ ዓለም ስንመላለስ የነበረው በንፁህ ህሊና እና ከእግዚአብሔር በሚሰጥ ቅንነት ነበር። በተለይም ከናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት የተመሰረተው በእግዚአብሔር ፀጋ ላይ እንጂ በምድራዊ ጥበብ ላይ አልነበረም። 13 ልታነቡትና ልትረዱት የማትችሉትን አንዳችም ነገር አንዳልፃፍንላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 14 እናንተም በከፊል እንደተረዳችሁን በጌታችን በኢየሱስ ቀን እናንተ በእኛ እንደምትመኩ እኛም እንዲሁ በእናንተ እንመካለን። 15 ስለዚህ ርግጠኛ ስለነበርሁ፥ በመጀመሪያ ወደናንተ መምጣት ፈለግሁ፤ ይህ ደግሞ በሁለቱም ጉብኝቶቼ ተጠቃሚዎች እንድትሆኑ ነው። 16 ወደ መቄዶንያ ስሄድ ልጎበኛችሁ ፤ከዚያ ደግሞ ክመቄዶንያ ስመለስ ላያችሁ፤በኋላ ግን እናንተው ወደ ይሁዳ እንደምትልኩኝ አቅጄ ነበር። 17 ይህንን ሳስብ ታዲያ የወላወልኩ ይመስላችኋልን? ወይስ በአንድ ጊዜ እንደ ሰው መስፈርት "አዎን፥ አዎን" እና "አይደለም፥አይደለም" በማለት አቀድኩን? 18 ነገር ግን እግዚአብሔር የታመነ እንደሆነ፣ እኛም በሁለት ቃል "አዎን" እና "አይደለም" ብለን አንናገርም። 19 ምክንያቱም በእናንተ መካከል በእኔ፥ በስልዋኖስ እና በጢሞቲዎስ የተሰበከው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በአንድ ጊዜ "አዎን" እና "አይደለም" አልነበረም፥ይልቅስ ሁልጊዜም በእርሱ "አዎን" ነው። 20 በእርሱ የእግዚአብሔር ተስፋዎች ሁሉ "አዎን" ናቸው። ስለዚህ እኛም በእርሱ በኩል ለእግዚአብሔር ክብር "አሜን" እንላለን። 21 እንግዲህ እኛንም ከእናንተ ጋር በክርስቶስ የሚያፀናን እንዲሁም የሾመን እግዚአብሔር ነው። 22 ለዚህም ወደፊት ለሚሰጠን ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን በልባችን የሰጠን ማህተሙንም ያደረገብን እርሱ ነው። 23 ሆኖም ግን ወደ ቆሮንቶስ ያልመጣሁት እንዳላሳዝናችሁ አስቤ እንደሆነ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። 24 እኛም እምነታችሁ ምን መምሰል እንዳለበት በናንተ ላይ ልናዝዝ ሳይሆን በእምነታችሁ ፀንታችሁ እንድትቆሙ ለደስታችሁ የምንሰራ ነን።