1 እግዚአብሔር ለራሱ ለለያቸው ሰዎች ሁሉ -- በኢየሩሳሌም ለሚገኙ አማኞች ስለሚደረገው ስለዚህ ገንዘብ ማሰባሰብ ተጨማሪ ምንም ነገር ልጽፍላችሁ በእርግጥ አያስፈልገኝም፡፡ 2 መርዳት እንደምትፈልጉ አስቀድሞ አውቄአለሁ፣ ደግሞም በመቄዶንያ አማኞች ፊት አመሰግኜአችኋለሁ፡፡ በእርግጥ እናንተና በአካይያ ክፍለ አገር የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለዚህ ማሰባሰብ እየተዘጋጃችሁ እንዳላችሁ ነግሬአቸዋለሁ፡፡ የእናንተ ጉጉት የመቄዶንያ አማኞችን እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳ ምሳሌ ሆኖአል፡፡ 3 ከእኔ በፊት ወንድሞችን ልኬአለሁ፣ ይኸውም ሲያገኟችሁ እናንተን ማመስገናችን በከንቱ እንዳልሆነ እንዲያዩ ነው፤ ደግሞም የተዘጋጃችሁ እንደሆናችሁ ለሌሎች እንደተናገርኩት፣ ይህን ሥራ ለማጠናቀቅ ዝግጅዎች እንድትሆኑ ከእኔ በፊት ላከኋቸው፡፡ 4 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስመጣ አንዳንድ የመቄዶንያ ሰዎች ምናልባት ከእኔ ጋር ይመጡ ይሆናልና፣ምናልባትም ለመስጠት የምትፈልጉትን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁዎች ሳትሆኑ ያገኟችሁ ይሆናል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ሳትዘጋጁ ብንመጣ ስለ እናንተ መልካም በመናገራችን እናፍራለን፣ እናንተም ደግሞ ታፍራላችሁ፡፡ 5 ለመስጠት ቃል ያገባችሁትን ገንዘብ ለመቀበል አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ እንዲያመቻቹ ወንድሞችን ወደ እናንተ ለመላክ የትኛውንም ጥረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ወስኜአለሁ፡፡ በዚህም ይህ ገንዘብ የምናስከፍላችሁ ግብር ሳይሆን በፈቀዳችሁ በነጻ የለገሳችሁት ይሆናል፡፡ 6 ፍሬ ነገሩ፣ ጥቂት ዘር የዘራ ማንም የሚሰበስበው ምርት ጥቂት ይሆናል፣ ነገር ግን ብዙ የዘራ ማንም ደግሞ ብዙ ይሰበስባል የሚል ነው፡፡ 7 አስቀድማችሁ ምን ያህል ገንዘብ እንደምትሰጡ በልባችሁ ወስኑ፣ በሰጣችሁ ጊዜም አትጸጸቱም፡፡ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳልና እንድትሰጡ ማንም እንዳስገደዳችሁ ሊሰማችሁ አይገባም፡፡ 8 እናተ ራሳችሁ ሁልጊዜ የሚያስፈልጋችሁ እንዲኖራችሁ ደግሞም በጎ ለማድረግ በቂ ነገር እንዲኖራችሁ እግዚአብሔር ሁሉንም ዓይነት ስጦታዎች አብዝቶ ይስጣችኋል፡፡ 9 በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ፡- “ለሰዎች በሁሉ ስፍራ መልካም ነገሮችን ይሰጣል፣ ለድኻም የሚያስፈልገውን ይሰጣል፡፡ እነዚህንም ለዘላለም ያደርጋል፡፡” 10 እግዚአብሔር ለሚዘራ ዘርን ይሰጣል፣ ለሚጋግረውም እንጀራን ይሰጣል፡፡ ዘርን ይሰጣችኋል ደግሞም ለሌሎች ልትሰጡ የምትችሉትን ያበዛላችኋል፡፡ 11 ለጋሶች እንድትሆኑ፣ እግዚአብሔር በብዙ መንገዶች ባለጠጎች ያደርጋአችኋል፡፡ በመጨረሻም እኛ ሐዋርያት በሠራነው ሥራ አማካይነት ስለተቀበሉት ሌሎች ብዙዎች እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ 12 ይህን ገንዘብ የምንቀበለው፣ በችግር ላይ ያሉትን ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ለመርዳት ብቻ አይደለም፣ ብዙ አማኞች እግዚአብሔርን ያመሰግኑት ዘንድም ነው፡፡ 13 ይህን ሥራ በመጀመራችሁ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆናችሁ አሳይታችኋል፡፡ ለእርሱ በመታዘዝና ስለክርስቶስ በምሥራቹ ቃል አማካይነት የተናገረውን በማመን እግዚአብሔርን አክብራችኋል፡፡ በልግስና በመስጠትም እርሱን አክብራችኋል፡፡ 14 እግዚአብሔር ለእናንተ ቸር ስለሆነበት ድንቅ አሠራሩ፣ የምትሰጡአቸው ዎች ሊያዩአችሁ በጣም ይናፍቃሉ፣ ስለ እናንተም ይጸልያሉ፡፡ 15 ከእርሱ ዘንድ ስለሆነው ስለዚህ ሥጦታ ለእግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን-- ሥጦታው በቃላት ልንገልጠው እስከማንችል ድረስ ታላቅ ነው፡፡