ምዕራፍ 1

1 መታመኛችን በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ እና በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ጳውሎስ፣ 2 በእምነት እውነታኛ ልጄ ለሆነው፣ ለጢሞቴዎስ፡፡ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን፡፡ 3 ወደ መቄዶንያን በሄደኩ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ልዩ ትምህርትን እናዳያስተምሩ፣ 4 በእምነት የሆነውን የእግዚአብሔርን እቅድ ለማያግዙ ለታሪኮችና መጨረሻ የሌላቸውን የትውልዶችን ሐረግ ለመቁጠር ትኩረት ወደ መስጠት እንዳያዘነብሉ ታስጠነቅቃቸው ዘንድ በኤፌሶን እንድትቀመጥ አዘዝኩህ፡፡ 5 ነገር ግን የትእዛዙ ግብ ከንጹህ ልብ፣ ከመልካም ኅሊና እና ከእውነተኛ እምነት የሚወጣ ፍቅር ነ|ው፡፡ 6 አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ርቀው ወደ ባዶ ወሬ ዞረዋል፡፡ 7 የሕግ አስተማሪዎች ለመሆን ተመኝተዋል፤ ነገር ግን የሚናገሩትንና መሆን አለበት የሚሉትን ነገር አያውቁትም፡፡ 8 ሆኖም ሕግ በትክክል ቢጠቀምበት መልካም እንደሆነ እናወቃለን፡፡ 9 እንዲሁም ሕግ ለጻድቅ ሰው እንዳልተሠራ እናውቃለን፤ ነገር ግን ሕግ የተሰጠው፣ ሕገወጥ ለሆኑና ለአመጸኞች ሰዎች ፣ እግዚአብሔርን ለማይፈሩና ለኃጢአተኞች ፣ 10 ለአመንዝሮችና ለግብረ ሰዶማውያን፣ ሰዎችን ባርያ አድርገው ለሚሸጡ፣ ለውሸተኞች፣ ለሐሰት ምስክሮች፣ ከእውነተኛው ትምህርት ርቀው ለሚገኙ ሰዎች ነው፡፡ 11 ይህ እውነተኛ ትምህርት በተባረከው አምላካችን ለእኔ በአደራ የተሰጠው ወንጌል ነው፡፡ 12 ለዚህ አገልገሎት ታማኝ እንድሆን ያበቃኝንና የሾመኝን፣ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግናለሁ፡፡ 13 ምንም እንኳ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ ብሆንም፣ ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግሁት ከጌታ ዘንድ ምሕረትን አግኝቼአለሁ፡፡ 14 ነገር ግን የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእምነትና ከፍቅር ጋር ይበልጥ በዛ፡፡ 15 ‹‹ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም መጣ›› የሚለው መልዕክት ሁሉም ሊቀበሉት የተገባና አስተማማኝ ነው፡፡ እኔም ከእነዚህ ሁሉ የባስኩ ኃጢአተኛ ነኝ፡፡ 16 በዚህም ምክንያት ከኃጢአተኞች ዋነኛ በምሆን በእኔ ክርስቶስ ኢየሱስ ትእግስቱን ሁሉ ሊያሳይ ምሕረትን አገኘሁ፤ ይህም የሆነው በእርሱ ለሚያምኑና የዘላለም ሕይወት ለሚያገኙ ምሳሌ እሆን ዘንድ ነው፡፡ 17 ስለዚህ ለዘላለም ንጉሥ ፣ ለማይሞተው እና ለማይታየው፣ ብቻውን አምላክ ለሆነው፣ ክብርና ግርማ ለዘላለም ይሁን፡፡ አሜን፡፡ 18 ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ስለ አንተ አስቀድሞ በተነገረው ትንቢት ተስማምቼ ይህን አዝሃለሁ፤ መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፤ 19 ስለዚህም እምነትና መልካም ኅሊና ይኑርህ፡፡ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ክደው መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋል፡፡ 20 ከእነዚህም መካከል በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል እንዳይናገሩ፣ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው፣ ሄሜኔዎስ እና እስክንድሮስ ይገኙባቸዋል፡፡