ምዕራፍ 1

1 ከጳውሎስ፣ ስልዋኖስና ጢሞቴዎስ በእግዚአብሔር አብና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉ ለተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን፤ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን! 2 በጸሎታቻን እያሳሰብን እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ስለ ሁላችሁም እናመሰግናለን። 3 በእምነት ስለምትሠሩት ሥራ፣ በፍቅር ስለምትደክሙት ድካምና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ በመታመን ስለመጽናታችሁ በእግዚአብሔር በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እናስታውሳችኋለን። 4 በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! መመረጣችሁን እናውቃለን፣ 5 ወንጌላችን በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፥ ነገር ግን በኃይል፣ በመንፈስ ቅዱስና በብዙ መረዳትም እንጂ፥ ስለእናንተ ስንል በመካከላችሁ ደግሞ እንዴት እንደነበርን ታውቃላችሁ። 6 በብዙ መከራ ውስጥ ቃሉን ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ስትቀበሉት እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፣ 7 በመቄዶንያ ሁሉና በአካይያ ላሉ ለሚያምኑት ምሳሌ ሆናችሁላቸዋል። 8 የጌታ ቃል ከእናንተ ተነሥቶ በመቄዶንያና አካይያ ብቻ ሳይሆን ምንም መናገር እስከማያስፈልገን ድረስ በእግዚአብሔር ላይ ያላችሁ እምነት በሁሉ ሥፍራ ተወርቷል። 9 እኛን በሚመለከት እንዴት ያለ አቀባበል እንዳደረጋችሁልን፣ ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ታገለግሉ ዘንድ ከጣዖታት እንዴት ወደ እግዚአብሔር ዘወር 10 እንዳላችሁ፣ደግሞም ከሰማይ የሚመጣውን ልጁን፣ ያም ከሙታን ያስነሳውን፣ ሊመጣ ካለው ቁጣ የሚያድነንን ኢየሱስን እንደምትጠባበቁ እነርሱ ራሳቸው ይመሰክራሉ።