ምዕራፍ 18

1 ለሳኦል መናገሩን በጨረሰ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ራሱ ነፍስ አድርጎ ወደደው። 2 በዚያ ቀን ሳኦል ዳዊትን ወደ ራሱ አገልግሎት ወሰደው፤ ወደ አባቱ ቤት እንዲመለስ አላሰናበተውም። 3 ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ ነፍስ አድርጎ ስለወደደው በመካከላቸው የወዳጅነት ቃል ኪዳን አደረጉ። 4 ዮናታን የለበሰውን ካባ አውልቆ ከጦር ልብሱ ጋር፥ እንዲሁም ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ለዳዊት ሰጠው። 5 ዳዊት ሳኦል ወደሚልከው ቦታ ሁሉ ይሄድ ነበር፥ ይከናወንለትም ነበር። ሳኦልም በተዋጊዎቹ ላይ ሾመው። ይህም በሕዝቡ ዓይን ሁሉ ደግሞም በሳኦል አገልጋዮች ፊት ደስ የሚያሰኝ ሆነ። 6 ፍልስጥኤማውያንን ድል አድርገው ወደ መኖሪያቸው በመመለስ ላይ እያሉ ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ንጉሥ ሳኦልን ለመገናኘት፥ ሴቶች በከበሮና በሙዚቃ መሳሪያዎች በደስታ እየዘመሩና እየጨፈሩ መጡ። 7 ሴቶቹም ሲጫወቱ እየተቀባበሉ ይዘምሩ ነበር፤ እነርሱም፥ "ሳኦል ሺዎችን ገደል፥ ዳዊትም ዐሥር ሺዎችን ገደለ" እያሉ ዘመሩ። 8 ሳኦል እጅግ ተቆጣ፥ ይህም መዝሙር አስከፋው። እርሱም፥ "ለዳዊት ዐሥር ሺዎች አሉ፥ ለእኔ ግን ሺዎችን ብቻ። ታዲያ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረው?" አለ። 9 ሳኦል ከዚያን ቀን ጀምሮ ዳዊትን በጥርጣሬ ዐይን ተመለከተው። 10 በቀጣዩ ቀን በሳኦል ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት። እርሱም በቤት ውስጥ እንደ ዕብድ ይለፈልፍ ነበር። ስለዚህ ዳዊት በየቀኑ ያደርግ እንደነበረው በገናውን ይደረድር ነበር። ሳኦልም በእጁ ጦር ይዞ ነበር። 11 ሳኦል፥ "ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ" ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት። ነገር ግን ዳዊት ከሳኦል ፊት ሁለት ጊዜ እንዲህ ባለ መንገድ አመለጠ። 12 እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንጂ ከእርሱ ጋር ስላልነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። 13 ስለዚህ ሳኦል ከፊቱ አራቀው፥ ሻለቃም አድርጎ ሾመው። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በሕዝቡ ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። 14 እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ ዳዊት የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለት ነበር። 15 እንደ ተከናወነለት ሳኦል ባየ ጊዜ እጅግ ፈራው። 16 ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱት። 17 ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፥ "ትልቋ ልጄ ሜሮብ ይቹት። እርሷን እድርልሃለሁ። ብቻ ጎብዝልኝ፥ የእግዚአብሔርን ጦርነቶችም ተዋጋ" አለው። ሳኦል፥ "እጄ በእርሱ ላይ አይሁን፥ ነገር ግን የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ይሁን" ብሎ አስቦአልና። 18 ዳዊትም ሳኦልን፥ "የንጉሥ አማች ለመሆን እኔ ማነኝ? ሕይወቴ ወይም የአባቴ ቤተ ሰብ በእስራኤል ውስጥ ምንድነው?" አለው። 19 ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤድሪኤል ተዳረች። 20 ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው። ለሳኦል ነገሩት፥ ይህም እርሱን ደስ አሰኘው። 21 ከዚያም ሳኦል፥ "ወጥመድ እንድትሆነውና የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ እንድትሆን እርሷን እድርለታለሁ" ብሎ አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ዳዊትን ለሁለተኛ ጊዜ፥ "አማቼ ትሆናለህ" አለው። 22 ሳኦል አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፥ "ዳዊትን በምስጢር እንዲህ በሉት፥ 'አስተውል፥ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፥ አገልጋዮቹም ሁሉ ይወዱሃል። እንግዲያው የንጉሡ አማች ሁን'" 23 ስለዚህ የሳኦል አገልጋዮች ይህንን ቃል ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም፥ "እኔ ድሃና ብዙም የማልታወቅ ሰው ሆኜ እያለሁ የንጉሥ አማች እንድሆን ማሰባችሁ ጉዳዩ እንዴት ቀልሎ ታያችሁ?" አላቸው። 24 የሳኦል አገልጋዮችም ዳዊት የተናገረውን ቃል ነገሩት። 25 ሳኦልም፥ "ለዳዊት እንዲህ ትሉታላችሁ፥ 'የንጉሡን ጠላቶች ለመበቀል ከአንድ መቶ የፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ብቻ በቀር ንጉሡ ምንም ጥሎሽ አይፈልግም''። ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ለማድረግ ሳኦል አሰበ። 26 አገልጋዮቹ ይህንን ቃል ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሡ አማች መሆን ዳዊትን ደስ አሰኘው። 27 እነዚያ ቀናት ከማብቃታቸው በፊት፥ ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሄዶ ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ። ዳዊት የንጉሡ አማች ይሆን ዘንድ ሸለፈቶቹን አመጣ፥ ለንጉሡም ሙሉውን ቁጥር አስረከቡ። ስለዚህ ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ዳረለት። 28 እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደነበረ ሳኦል አየ፥ ዐወቀም። የሳኦል ልጅ ሜልኮልም ወደደችው። 29 ሳኦልም ዳዊትን የበለጠ ፈራው። ሳኦል የዳዊት ጠላቱ እንደሆነ ቀጠለ። 30 ከዚያም የፍልስጥኤም ልዑላን ብዙ ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው ለጦርነት መጡ፥ ዳዊት ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ በበለጠ ሁኔታ የተሳካለት ሆነ፥ በመሆኑም ስሙ እጅግ የተከበረ ሆነ።