ምዕራፍ 14

1 አንድ ቀንም ዮናታን መሣሪያውን የሚይዝለትን ጎልማሳ፡- “ከእኔ ጋር ና፣ ፍልስጥኤማውያን ወታደሮች ድንኳናቸውን ወደ ተከሉበት ስፍራ እንሻገር” አለው፡፡ ስለዚህ ተያይዘው ሄዱ፣ዳሩ ግን ምን ሊሰሩ እንደሆነ ዮናታን ለአባቱ አልነገረውም፡፡ 2 በዚያም ቀን ሳኦልና ከእርሱ ጋር የነበሩ ስድስት መቶ ወታደሮች ሰዎች እህል በሚወቁበት ጊብዓ ባለው በሮማኑ ዛፍ ዙሪያ ተቀምጠው ነበር፡፡ 3 ቅዱሱን ኤፉድ ከሚለብሱት አንዱ ካህኑ አኪያም ደግሞ እዚያው ነበር፡፡ አኪያም የኢካቦድ ወንድም የሆነው የአኪጦብ ልጅ ነው፡፡ ኢካቦድና አኪጦብ ደግሞ በሴሎ የጌታ እግዚአብሔር ካህን ሆኖ ያገለገለ የዔሊ ልጅ የሆነው የፊንሐስ ልጆች ነበሩ፡፡ ዮናታን የእስራኤላውያንን ሰፈር ትቶ እንደ ሄደ ማንም አላወቀም። 4 ዮናታንም እራሱና ጎልማሳው ፍልስጥኤማውያን ወታደሮች ወደ ሰፈሩበት ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል እንዲሄዱ ወሰነ፡፡ በአንደኛው መተላለፊያ ስም ቦዜዝ/ቦጼጽ የሁለተኛውም መተላለፊያ ስም ደግሞ ሴኔህ ሲሆን በዚህም ስፍራ ሁለት ሾጣጣ ደንጊያዎች ነበሩ። 5 አንዱም ሾጣጣ ደንጊያ በሰሜን በኩል ወደ ማክማስ አንጻር ሲመለከት፥ በሌላኛው አቅጣጫ የሚገኘው ሾጣጣ ደንጊያ ደግሞ በደቡብ በኩል ወደ ጌባ/ጊብዓ ይመለከት ነበር። 6 ዮናታንም መሣሪያውን የሚይዝለትን ጎልማሳ፡- “ከእኔ ጋር ና፡፡ እነዚያ አረማውያን ድንኳናቸውን ወደ ተከሉበት ስፍራ እንሂድ፡፡ ምናልባትም ጌታ እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል፡፡ ሁለት ሰዎች ብቻ መሆናችን ወይም ብዙዎች ምንም ለውጥ አይኖረውም፤ እኛ እነርሱን እንድናሸንፍ ለማስቻል ጌታ እግዚአብሔርን የሚያግደው አንዳችም ነገር አይኖርም” አለው፡፡ 7 የዮናታንን መሣሪያዎች የያዘው ጎልማሳ ሰውም፦ “ልናደርገው የሚገባ የላቀው ነገር ብለህ የምታስበውን አድርግ፡፡ እኔ ልረዳህ ከአንተ ጋር ነኝ፡፡” 8 ዮናታንም፦ በጣም ጥሩ፣ ከእኔ ጋር ና፡፡ የፍልስጥኤም ሰራዊት ወዳሉበት ወደማዶ ሸለቆውን ተሻግረን እንሂድ፣ ደግሞም እንዲመለከቱን እናድርግ፡፡ 9 እነርሱም፦ ‘እናንተ ሁለታችሁ ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ’ ቢሉን፣ ባለንበት ቦታ እንቆያለን እንጂ ወደ እነርሱ አንወጣም፡፡ 10 ነገር ግን፦ ‘ወደ ላይ ውጡ’ ቢሉን ጌታ እግዚአብሔር እነርሱን ማሸነፍ እንድንችል እንዳደረገን ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ ወደ ላይ ወጥተን እንወጋቸዋለን፡፡ 11 ሁለቱም ሸለቆውን ሲያቋርጡም፣ ፍልስጥኤማውያን ወታደሮች ወደ እነርሱ እየመጡላቸው መሆኑን ተመለከቱ፡፡ እነርሱም፦ ተመልከቱ! ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጕድጓድ እየወጡ ናቸው ተባባሉ፡፡ 12 ከዮናታንንና መሳሪያ ከሚይዝለት ጎልማሳ አቅራቢያ ያሉ የፍልስጥኤም ወታደሮች፦ “ወደዚህ ውጡ፥ ስለ መዋጋት እንዴት እደሆነም አንድ ነገር እናስተምራችኋለን!” አሏቸው። ዮናታንም ከእርሱ ጋር ለነበረው ጎልማሳ፡- “ከኋላዬ ተከትለኸኝ ወደ ላይ ውጣ፣ ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር እነርሱን እናሸንፍ ዘንድ ሊረዳን ነውና!” 13 ስለዚህ ዮናታን ቦታው በጣም ገደላማ በመሆኑ እጁንና እግሩን ተጠቅሞ ወደ ላይ ወጣ፡፡ ጎልማሳው ሰውም እርሱን ተከትሎ ወደ ላይ ወጣ፡፡ ዮናታን ወደ ላይ እየወጣ ሳለ ብዙ ፍልስጥኤማውያን ወታደሮችን መትቶ ገደላቸው፣ አብሮት የነበረው ጎልማሳ ሰውም ከዮናታን ጀርባ እየተከተለ ሌሎች ብዙዎችን ገደለ፡፡ 14 በዚያ መጀመሪያ ውጊያም ሁለቱ አብረው ሃያ ግድም የፍልስጥኤም ወታደሮችን ግማሽ ሄክታር በሆነ ሥፍራ ላይ ገደሉ፡፡ 15 ሌሎቹ የፍልስጥኤም ወታደሮች በሙሉ፣ በጦር ሰፈሩ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች፣ የእስራኤልን ከተሞች ያጠቁ የነበሩ አንዳንዶች፣ በቅርብ ርቀት ባለ እርሻ የነበሩ አንዳንዶች፣ተሸበሩ፡፡ እግዚአብሔርም ምድሪቱ እንደትናወጥ አደረጋት፤ እነርሱ ሁሉም ተሸበሩ፣ፈሩ፡፡ 16 የሳኦል መመልከቻ ማማዎች/ቃኚዎች የነበሩት የብንያም ነገድ አውራጃ በሆነችው ጊብዓ ነው፡፡ እነርሱም የፍልስጥኤም ሰራዊት ወታደሮች በሁሉም አቅጣጫ ሲሸሹ ተመለከቱ፡፡ 17 ሳኦልም ጥቂት ወታደሮቹ የፍልስጥኤምን ሰራዊት እንደ መቱ አረጋገጠ፡፡ ስለዚህም ከእርሱ ጋር የነበሩ ወታደሮቹን፡- “ከእኛ ሰዎች መካከል እዚህ የሌሉ ቢኖሩ አረጋግጡ” አላቸው፡፡እነርሱም ቆጥረው ባረጋገጡ ጊዜ ዮናታንና መሣሪያውን የሚይዝለት ሰው በዚያ አልነበሩም። 18 ሳኦልም ካህኑን አኪያን፦ “ኤፉድን አምጣና ምን ማድረግ እንደሚገባን እንጠይቅ” አለው። በዚያም ቀን አኪያ ቅዱሱን ኤፉድ ለብሶ ከእስራኤላውያን ጋር ይጓዝ ነበር፡፡ 19 ዳሩ ግን ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር ፣የፍልስጥኤማውያን ወታደሮች በጎላ ሁኔታ ሲታወኩ ተመለከተ፡፡ ሳኦልም አኪያንን፦ “እጅህን ከተቀደሰው ኤፉድ ላይ አንሳ” አለው። 20 ሳኦልም ሕዝቡን ሰብስቦ ወደ ውጊያው ግንባር ሄዱ፡፡ ሲደርሱም፥ ፍልስጥኤማውያን ወታደሮች በጣም ግራ ተጋብተው በያዙት ሰይፍ እርስ በእርሳቸው ይሰያየፉ ነበረ፡፡ 21 ቀድሞ ጥቂት የዕብራውያን ሰዎች ከፍልስጥኤም ሰራዊት ጋር ወግነው የራሳቸውን ሰራዊት ከድተው ነበረ፡፡ አሁን ግን እነዚያ ሰዎች አምጸው/ዞረው ሳኦልን፣ ዮናታንንና ሌሎች እስራኤላውያን ወታደሮችን ተቀላቀሉ፡፡ 22 ጥቂት የእስራኤላውያን ወታደሮች ቀደም ብሎ ሸሽተው የኤፍሬም ነገዶች በሚኖሩበት ተራራማ አገር ተሸሸገው ነበረ፡፡ የፍልስጥኤም ወታደሮች እየፈረጠጡ መሆኑን ሲሰሙ፣ ከተራራው ወርደው የእስራኤልን ወታደሮች በመቀላቀል ፍልስጥኤማውያን ወታደሮችን ያሳድዱ ጀመሩ፡፡ 23 በዚያ ቀን ጌታ እግዚአብሔር እስራኤልን አዳነ፡፡ የእስራኤል ወታደሮችም ጠላቶቻቸውን ከቤትአዌን ከተማ ባሻገር ማሳደድን ቀጠሉ፡፡ 24 የሳኦል ወታደሮች ወደ ጦርነት ከመሄዳቸው በፊት፣ሳኦል በመሃላ “ማናችሁም ብትሆኑ ጠላቶቻችንን በሙሉ ከማሸነፋችን በፊት የትኛውንም ዓይነት ምግብ ጀንበር ሳትጠልቅ እንድትቀምሱ አልፈልግም፡፡ ማንም አንዳች ቢቀምስ ፣ጌታ እግዚአብሔር ይረግመዋል” አላቸው፣ ምክንያቱም ተርበው ነበርና፡፡ 25 የእስራኤል ሰራዊት ሁሉ ወደ ጫካው ገባ፤ በምድር ላይም የማር እንጀራ አገኙ። ይሁንና አንዳችም አልበሉም፡፡ 26 ምንም ምግብ ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ ስላደረጉ አንዳችም ለመብላት ፈሩ፡፡ 27 . ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን በጽኑ መሀላ ማሰሩን አልሰማም ነበር፡፡ ዮናታን የጦር ሰፈሩን እጅግ ማልዶ በጧት ስለለቀቀ ማር እንጀራውን ሲመለከት በእጁ ያለችውን በትር ጫፍዋን ወደ ወለላው ነከረ፥ ጥቂት ማርም በላ፡፡ ማሩን ከበላም በኋላ ጥንካሬ ተሰማው፡፡ 28 ሆኖም ከእስራኤል ሰራዊት አንዱ ሲበላ ተመልክቶት፡- “አባትህ ዛሬ ምንም ዓይነት መብል የሚበላ ሰው ቢኖር፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲረግመን በጥብቅ መሀላ አስገብቶናል፡፡” ስለዚህ አሁን እኛ እረሱን በመታዘዛች ስለራበን በጣም ድካምና ዝለት አግኝቶናል” አለው። 29 ዮናታንም፦ አባቴ ሁላችንንም አስቸገረ፤ ጥቂት ማር ስለበላሁ እንዴት እንደታደስሁ ተመልከቱ!። 30 ሁላችንም ጠላቶቻችንን ስናሳድድ ከእነርሱ የነጠቅነውን ምግብ እንድንበላ ፈቅዶልን ቢሆን ኖሮ እስካሁን ከገደልናቸው ወታደሮች ይልቅ በገደልን ነበር” አለ 31 በዚያም ቀን እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ ከተማ እስከ ምዕራቡ አይጆሎን/ኤሎን ድረስ አሳድደው ገደሏቸው፡፡ እነርሱ ግን ከረሃብ የተነሳ ድካማቸው በረታ፡፡ 32 እነርሱም ፍልስጥኤማውያን ትተው የሸሹትን ብዙ በጎችና መንጋም ወሰዱ፡፡ እጅግ ተርበው ስለነበረ፣ ከእነዚያ እንስሳት ጥቂቱን አርደው ደሙን ከእንስሳቱ ሳያፈስሱ በሉ። 33 ከወታደሮቹም አንዱ ለሳኦል፦ “ተመልከት፣ሕዝቡ ሥጋውን ከደሙ ጋር በመብላት በጌታ እግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ” ብሎ ነገረው። ሳኦልም፦ እጅግ ተላለፋችሁ፤ አሁንም ትልቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ አቅርቡልኝ አላቸው። 34 ያንንም ካደረጉ በኋላ፣ ለእነዚያ ሰዎች እንዲህ አላቸው፣ “ሄዳችሁ ለሁሉም ወታደሮች እያንዳንዳቸው አንድ በሬ ወይም በግ ወደ እኔ እንዲያመጡና በዚህ ደንጊያ ላይ አርደው ሥጋውን ከመብላታቸው በፊት ደሙን እንዲያፈስሱ ንገሩ ፡፡ የአንዳንድ እንስሳትን ሥጋ ከደሙ ጋር በመብላት በጌታ እግዚአብሔር ላይ ኃጢአት መሥራት አይኖርባቸውም” አላቸው፡፡ በዚያም ምሽት ወታደሮቹ በሙሉ እንስሳትን አምጥተው በዚያ አረዱ፡፡ 35 ያኔም ሳኦል ጌታ እግዚአብሔርን ያመልክ ዘንድ መሰዊያ ሠራ፡፡ ለጌታ እግዚአብሔር መሰዊያ ሲሠራ ይህ መጀመሪያው ነበር፡፡ 36 ሳኦልም ለእስራኤል ወታደሮች፦ “በዚህ ምሽት ፍልስጥኤማውያን ወታደሮችን እናሳድድ፡፡ ሌሊቱን ሁሉ ጥቃት ልንፈጽምባቸው እንችላለን፡፡ ከእነርሱ ማናቸውም ቢሆን በሕይወት እንዲያመልጥ አንፈቅድለትም” አላቸው፡፡ የእስራኤል ወታደሮችም፡- “እናደርገው ዘንድ የተሻለ ነው ብለህ የምታስበውን ማናቸውንም ነገር እናደርጋለን” ሲሉ መለሱለት፡፡ ካህኑ ግን “ምን ማድረግ እንደሚገባን አሳቡን ለማወቅ ጌታ እግዚአብሔርን እንጠይቅ” አላቸው፡፡ 37 ሳኦልም፦ “ፍልስጥኤማውያንን እንከተል? እናሸንፋቸው ዘንድ ታስችለናለህ?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀው። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በዚያን ቀን ለሳኦል አልመለሰም። 38 ሳኦል ም ሁሉንም የሰራዊቱን መሪዎች ጠርቶ፦ “እግዚአብሔር ያልመለሰልኝ አንድ ሰው ኃጢአት በመሥራቱ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ያ ሰው የፈጸመው ኃጢአት ምን እንደሆነ ፈልገን ማግኘት አለብን፡፡ 39 ጌታ እግዚአብሔር ከፍልስጥኤም ሰራዊት አድኖናል፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሕያው መሆኑ እርግጠኛ እንደሆነ ሁሉ፣ ኃጢአትን የሠራው ማንም ቢሆን ይሞታል፡፡ ኃጢአቱን የፈጸመው ልጄ ዮናታን ቢሆን እንኳ ይሞታል” አለ። ሕዝቡም በደለኛው ማን እንደሆነ ያውቁ ስለነበረ አንዳቸውም ለሳኦል ምንም አልመለሱለትም፡፡ 40 ሳኦልም ለእስራኤል ወታደሮች ሁሉ፦ “እናንተ በአንድ ወገን ቁሙ፡፡ ልጄ ዮናታንና እኔም በሌላ ወገን እንቆማለን” አለ። ሕዝቡም፡- የተሻለ ነው ብለህ የምታስበውን አድርግ” አሉት። 41 ሳኦልም ወደ እስራኤል አምላክ ጌታ እግዚአብሔር፦ “በደለኛው ማን እንደሆነና እንዳልሆነ ንገረኝ” ብሎ ጸለየ፡፡ ካህኑም ዕጣዎች፣ እጣዎቹም በደለኛው ከዮናታንና ከሳኦል አንዱ እንጂ ሌሎቹ ሰዎች ያለመሆናቸውን አመለከቱ፡፡ 42 ሳኦልም ካህኑን፦ “ጠጠሮቹን እንደገና ጥለህ ከሁለታችን ማን በደለኛ መሆኑን እንዲያመለክት አድርግ” አለው፡፡ እርሱም እንዲሁ አደረገ፣ ጠጠሮቹም በደለኛው ዮናታን እንደ ነበረ አመለከቱ፡፡ 43 ሳኦልም ዮናታንን፦ “ያደረግኸውን ስህተት ሆነ ነገር ንገረኝ” አለው፡፡ ዮናታንም፦ ጥቂት ማር በልቻለሁ፡፡ እርሷም በበትሬ ጫፍ ላይ የተቆነጠረች ጥቂት ነበረች፡፡ ያንን በማድረጌ ምክንያት ሞት ይገባኛል?” ብሎ ጠየቀው። 44 ሳኦልም፦ “አዎን መሞት አለብህ! ያንን በማድረግህ ካልተገደልህ እግዚአብሔር ቀስፎ እንደሚገድለኝ አስባለሁ! አለው፡፡ 45 የእስራኤል ወታደሮች ግን ሳኦልን፦ “ ዮናታን ለእኛ ለእስራኤላውያን በሙሉ ታላቅ ድል አሸንፏል፡፡ ጥቂት ማር በመብላቱ ሊገደል ይገባል? ዛሬ ዮናታን የፍልስጥኤምን ሰራዊት ብዙ ወታደሮች እንዲገድል እግዚአብሔር ስለረዳው፣ እንደ እውነቱ ከሆነ አይደረግም! ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ ሕያው እንደሆነ ሁሉ፣ እርሱን በማናቸውም ሁኔታ ትጎዳው ዘንድ አንፈቅድልህም” አሉት፡፡ ያንንም በመናገር የእስራኤል ወታደሮች ዮናታንን አዳኑት፣ ከሞትም ተረፈ። 46 ሳኦልም ወታደሮቹ ፍልስጥኤማውያንን ማሳደድ እንዲያቆሙ አዘዘ፣ፍልስጥኤማውያንም ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ሄዱ። 47 ሳኦልም ገዢ ከሆነ በኋላ፣ በሁሉም አቅጣጫ ከሚነሱ ጠላቶች ጋር ተዋጋ፡፡ ከአሞን ሕዝቦች፣ ከኤዶማውያን፣ ከሱባም ነገሥታት፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ይዋጋ ነበር፡፡ የእስራኤል ሰራዊት በሚዋጋበት ስፍራ ሁሉ ጠላቶቻቸውን ድል ይነሡ ነበር። 48 የሳኦል ሰራዊት ጀግንነት ተዋግቶ፥ በጣም ረጃጅም የሆኑትን አማሌቃውያን ትውልድ አሸነፈ፡፡ ሰራዊቱም እስራኤልን ይዘርፉት ከነበሩ ዘራፊዎቹ ጥቃት አዳነ። 49 የሳኦልም ወንዶች ልጆች ዮናታን፥ ኢሽቦሼት/የሱዊና ማልቺሹዋ/ሜልኪሳ ነበረ፡፡ እንዲሁም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፣ ስማቸውም ሜሮብ፥ የታናሺቱም ስም ሜልኮል ነበረ። 50 የሳኦልም ሚስት የአኪማአስ ሴት ልጅ አኪናሆም ነበረች፡፡ የሳኦል ሠራዊት አለቃ የሳኦል አጎት የኔር ልጅ የሆነው አበኔር ነበረ። 51 የሳኦልም አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር የአቢኤል ልጅ ነበሩ። 52 ሳኦል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ የእርሱ ሠራዊት ፍልስጥኤማውያን ወታደሮች ጋር ይዋጋ ነበረ፡፡ ሳኦልም ጎበዝ ወይም ጠንካራ ሰው ባየ ጊዜ ወደ እርሱ ሠራዊት እንዲቀላቀል ያስገድደው ነበር።