ምዕራፍ 1

1 የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኝነት ለሚኖሩ፤ ለተመረጡት፤ 2 እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ ቅዱስ ለተቀደሱት፤ ጸጋ ለእናንተ ይሁን፤ ሰላማችሁም ይብዛ። 3 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በመነሣቱ ምክንያት ላገኘነው ርስት ዋስትና እንዲሆነን በታላቅ ምሕረቱ አዲስ ልደትን ሰጠን፤ 4 ይህም የማይጠፋ፣ የማይበላሽ እና የማያረጅ ርስት በመንግሥተ ሰማይ ተጠብቆላችኋል። 5 እናንተም በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀው መዳን በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኅይል ተጠብቃችኋል። 6 ምንም እንኳን አሁን በብዙ ልዩ ልዩ ዐይነት መከራ ማዘናችሁ ተገቢ ቢሆንም፣ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። 7 ይኸውም፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እንዲፈተን ነው። ይህ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ አምነታችሁ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። 8 ኢየሱስ ክርስቶስን ባታዩትም እንኳ ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ ሊነገር በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት በጣም ደስ ይላችኋል፤ 9 አሁን የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ ነውና። 10 እናንተ ስለምትቀበሉት ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ይፈልጉና በጥልቅ ይመረምሩ ነበር፤ 11 የሚመጣው መዳን ምን ዐይነት እንደ ሆነ ለማወቅ ይመረምሩ ነበር፤ እንዲሁም በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራና ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ የተናገራቸው በምን ጊዜና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። ነቢያቱ ያገለግሉ የነበሩት እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳልነበረ ተገልጦላቸዋል፤ 12 ይኸውም ከሰማይ በተላከው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወንጌልን ያበሠሩአችሁ ሰዎች የነገሩአችሁን በመግለጥ ነው፤ መላእክትም እንኳ ይህ ነገር ሲገለጥ ለማየት ይመኙ ነበር። 13 ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጠቁ፤ ጠንቃቆች ሁኑ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በምታገኙት ጸጋ ላይ ፍጹም መተማመን ይኑራችሁ። 14 ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ ባለማወቅ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። 15 ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ፣ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ 16 ምክንያቱም «እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» ተብሎ ተጽፎአል። 17 ሳያዳላ በእያንዳንዱ ሰው ላይ እንደየሥራው የሚፈርደውን «አባት» ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በእንግድነት ዘመናችሁ እርሱን በማክበር ኑሩ። 18 ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር ማለትም በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ 19 ይልቁንም የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። 20 ክርስቶስ የተመረጠው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ነው፤ አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ለእናንተ ተገለጠ። 21 በእርሱ አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ። ይኸውም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን ነው። 22 ለእውነት በመታዘዝ ለእውነተኛ የወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልብ አጥብቃችሁ ተዋደዱ። 23 ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ ነገር ግን በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው። 24 ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ 25 የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። የተሰበከላችሁም ወንጌል መልእክቱ ይህ ነው።