ምዕራፍ 3

1 ሰሎሞን የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ሴት ልጅ በማግባት ከንጉሡ ጋር ወዳጅነት መሠረተ። የፈርዖንንም ልጅ አምጥቶ ቤተ መንግሥቱን፣ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅጥር ዙሪያውን ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አኖራት። 2 በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደሱ ገና አልተሠራም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በየኮረብታው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። 3 ሰሎሞን እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፤ የአባቱንም የዳዊትን መመሪያ ይጠብቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንስሶችን እያረደ በተለያዩ ኮረብቶች ላይ መሥዋዕት ያቀርብና ዕጣንም ያጥን ነበር። 4 ታላቅ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለነበር አንድ ቀን ንጉሥ ሰሎሞን መሥዋዕት ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ። በዚያም መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። 5 እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና ምን እንድሰጥህ ትፈልጋህ? ጠይቅ አለው። 6 ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፡- አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት፣ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን አሳይተኸዋል። ዛሬም በእርሱ ፈንታ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል። 7 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ እነሆ እኔ በዕድሜዬ ልጅ ብሆንም በአባቴ ቦታ ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል። እኔም መግባትንና መውጣትን የማልችል ነኝ። 8 እነሆ፣ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቆጠር በማይችል ሕዝብ መካከል አለሁ። 9 ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በማስተዋል በትክክኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ። ይህ ካልሆን ይህን ታላቅ ሕዝብህን ሊመራ ማን ይችላል? 10 ይህ የሰሎሞን ጥያቄ እንግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ 11 ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለው፡- ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ጠይቀሃል። 12 እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደ ፊት ሊያገኘው ከሚችለው የሚበልጥ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ። 13 ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ ሰጥቼሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማናቸውም ንገሥታት ያላገኙትን ብጽግናና ክብር አሰጥሃለሁ። 14 አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድ ለእኔም ብትታዘዝ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃሁ። 15 ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ ከዚህም በኋላ ለአገልጋዮቹ ሁሉ ግብዣ አደረገ። 16 አንድ ቀን ሁለት ሴተኛ አዳሪዎች መጥተው በሰሎሞን ፊት ቀረቡ፡፡ 17 ከእነርሱም አንደኛይቱ እንዲህ አለች ንጉሥ ሆይ ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን ስንኖር፣ በዚያውም በምንኖርበት ቤት ወንድ ልጅ ወለድኩ። 18 እኔ በወለድኩ በሦስተኛው ቀን እርስዋም ወንድ ልጅ ወለደች። በዚያ ቤት ውስጥ ከሁለታችን በቀር ሌላ ማንም አልነበረም። 19 ከዕለታት አንድ ቀን ሌሊት በላዩ ላይ ተኝታበት ስለ ታፈነ ልጇ ሞተ። 20 እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሌሊት ተነሥታ ታቅፌው የተኛሁትን ልጄን ወስዳ በእርስዋ አልጋ ላይ ካስተኛች በኋላ የሞተውን ልጅዋን አምጥታ በእኔ አልጋ ላይ በጎኔ አስተኛችው። 21 በማግስቱ ማለዳ ተነሥቼ ልጄን ለማጥባት ስዘጋጅ ሞቶ አገኘሁት፤ ትኩር ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብኩ። 22 ሁለተኛይቱ ሴት ግን አይደለም፣፣ በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፣ የሞተው ግን የአንቺ ነው አለች። የመጀመሪያይቱ ሴት አይደለም የሞተው የአንቺ ነው፤ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው አለች። በዚህ ዓይነት በንጉሡ ፊት ተከራከሩ። 23 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን አንደኛዋ በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፣ የሞተው ግን የአንቺ ነው ትላለች፤ ሌላይቱም ደግሞ አይደለም የአንቺ ልጅ ሞቶአል፤ የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው ትላታለች አለ። 24 ንጉሡም ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ፤ ሰይፍም አመጡለት። 25 በሉ እንግዲህ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ቁረጡና ለእያንዳንዱ ሴት ግማሽ አካሉን ስጡ ሲል አዘዘ፡፡ 26 እውነተኛይቱ ግን ለልጅዋ በመራራት አዝና ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ ልጁን አትግደለው፤ ለእርስዋ ይሰጣት አለች። ሌላይቱ ሴት ግን፣ ለእኔም ለእርስዋም አይሁን፤ ለሁለት ይቆረጥ አለች። 27 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ሕፃኑን አትግደሉት፤ እውነተኛይቱ እናት እርስዋ ስለሆነች ለመጀመሪያይቱ ሴት ስጡአት ሲል አዘዘ። 28 እስራኤላውያን ይህን የፍርድ ውሳኔ በሰሙ ጊዜ ሰሎሞን የሕዝብ ጉዳዮችን በትክክለኛ ፍርድ የሚወስንበትን ጥበብ እግዚአብሔር የሰጠው መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ታላቅ አክብሮት ሰጡት።