ምዕራፍ 1

1 ንጉስ ዳዊትም ሸምግሎ እና እድሜውም ገፍቶ ነበር። ምንም እንካ ልብስ ቢድርቡለትም፣ ሊያሞቀው አልቻለም። 2 ስለዚህ አገልጋዮቹ፣ "ለንጉስ አንዲት ወጣት ልጃገረድ እንፈልግለት እና ታገልግለው ትንከባከበውም። ንጉሱም እንዲሞቀው ክንዱ ውስጥ ትተኛ፣' አሉት። 3 ስለዚህም አንዲት ቆንጆ ልጃገረድ ለማግኘት በመላው እስራኤል ፈለጉ። ሱነማዊቱን አቢሳን አገኙ፤ ወደ ንጉሡም አመጡአት። 4 እርስዋም እጅግ ውብ ነበረች፤ እርስዋም ንጉሡን አገለገለችው፣ ተንከባከበችውም፤ ነገር ግን ንጉሡ ከእርስዋ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት አላደረገም። 5 በዚያን ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ “ንጉሥ እሆናለሁ” በማለት ራሱን ከፍ አደረገ። ስለዚህ በፊቱ የሚሮጡ ሃምሳ ፈረሰኞችንና ሠረገሎችን ለራሱ አዘጋጀ። 6 አባቱም ይህን ወይም ያንን ለምን ታደርጋለህ ብሎ ገስጾት አያውቅም ነበር። አዶንያስም ከአቤሴሎም በኋላ የተወለደ፣ እጅግ መልከ መልካም ነበር። 7 እርሱም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር አሤረ፤ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ረዱት። 8 ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅ፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ነቢዩ ናታን፣ ሳሚ፣ ሬሲምና ዳዊትን የሚደግፉ ኃያላን አዶንያስን አልተከተሉትም። 9 አዶንያስም ዓይንሮጌል አቅራቢያ ባለው በዞሔሌት ድንጋይ ላይ በጎችን፣ በሬዎችንና የሰቡ ወይፈኖችን ሠዋ። እርሱም፣ የንጉሡን ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፣ የይሁዳን ሰዎች ሁሉና የንጉሡን አገልጋዮች ጋበዛቸው። 10 ነገር ግን ነቢዩ ናታንን፣ በናያስን፣ ኃያላን ሰዎችን፣ ወይም ወንድሙን ሰሎሞንን አልጋበዛቸውም። 11 ከዚያም ናታን፣ ለሰሎሞን እናት ለቤርሳቤህ እንዲህ ሲል ነገራት፦ “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ መንገሡን አልሰማሽምን? 12 ስለዚህ የራስሽንና የልጅሽን የሰሎሞንን ሕይወት ለማትረፍ እንድትችዪ ልምከርሽ። 13 ወደ ንጉሥ ዳዊት ሂጂ፤ እንዲህም በዪው፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ’ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ ለአገልጋይህ ምለህልኝ አልነበረምን? ታዲያ አዶንያስ የሚነግሠው ለምንድን ነው?”። 14 በዚያም ከንጉሡ ጋር በመነጋገር ላይ እያለሽ እኔም ካንቺ በኋላ እገባና የተናገርሽው ሁሉ እውነት መሆኑን አረጋግጣለሁ” አላት፡፡ 15 ስለዚህ ቤርሳቤህ ወደ ንጉሡ ክፍል ሄደች። ንጉሡ እጅግ ስለ ሸመገለ ሱነማይቱ አቢሳ ታገለግለው ነበር። 16 ቤርሳቤህም ራስዋን ዝቅ አድርጋ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም፣ “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት፡፡ 17 እርሷም እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፣ ለአገልጋይህ፣ ‘በእርግጥ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለህ በአምላክህ በጌታ እግዚአብሔር ስም ምለህ ነበር፡፡ 18 ይኸው አሁን አዶንያስ ነግሦአል፤ አንተም ጌታዬ ንጉሡ ይህንን አታውቅም። 19 ስለዚህ በሬዎችን፣ የሰቡ ኮርማዎችንና ብዙ በጎች ሠውቷል። ደግሞም የንገሡን ልጆች፣ ካህኑን አብያታርንና የሠራዊቱን አዛዥ ኢዮአብን ጋብዟቸዋል፤ አገልጋይህን ሰሎሞንን ግን አልጋበዘውም፡፡ 20 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከአንተ ከጌታዬ በኋላ በዙፋንህ የሚቀመጠው ማን መሆኑን አንድታስታውቀው በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ 21 አለበለዚያ ግን ጌታዬ ንጉሡ ከአባቶቹ ጋር በሚያንቀላፋበት ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ወንጀለኛ እንቆጠራለን። 22 እርስዋ ለንጉሡ በመናገር ላይ እያለች ነቢዩ ናታን ገባ። 23 አገልጋዮቹም ለንጉሡ፣ “ነቢዩ ናታን እዚህ ነው” ብለው ነገሩት። እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በቀረበ ጊዜ በግምባሩ ምድር ላይ በመደፋት ለንጉሡ ሰላምታ አቀረበ። 24 ናታንም፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ ‘አዶንያስ ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ይቀመጣል’ ብለሃልን? 25 እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችን፣ የሰቡ ጥጆችንና በጎችን ሠውቷል፤ ደግሞም የንጉሡን ልጆች ሁሉ፣ የሠራዊቱን አዛዥ ኢዮአብንና ካህኑን አብያታርን ጋብዟል። ንጉሥ አዶንያስ ለዘላለም ይኑር! በማለት በፊቱ በመብላትና በመጠጣት ላይ ናቸው፡፡ 26 ነገር ግን እኔን አገልጋይህን፣ ካህኑን ሳዶቅን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስንና አገልጋይህን ሰሎሞንን ወደ ግብዣው አልጠራንም። 27 ከአንተ በኋላ በዙፋንህ ላይ የሚቀመጠው ማን እንደሆነ ለእኛ ለአገልጋዮችህ ሳትነግረን ይህንን ያደረግኸው ጌታዬ ንጉሡ ነህን?” 28 ከዚያም ንጉሡ ዳዊት፣ “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ” አለ። እርስዋም ንጉሡ ወዳለበት መጥታ በፊቱ ቆመች። 29 ንጉሡም ማለና፣ “ከደረሰብኝ መከራ ሁሉ የታደገኝ ጌታ እግዚአብሔር ሕያው የመሆኑን ያህል፤ 30 ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፣ በዙፋኔም ላይ በእኔ ቦታ ይቀመጣል’ ብዬ በእስራኤል አምላክ በጌታ እግዚአብሔር ስም የማልኩትን መሓላ ዛሬ እፈጽመዋለሁ” አላት። 31 ቤርሳቤህም ወደ መሬት በግንባሯ በመደፋት ለንጉሡ አክብሮቷን ካሳየች በኋላ፣ “ጌታዬ ንጉሡ ዳዊት ለዘለዓለም ይኑር!” አለች። 32 ንጉሥ ዳዊትም፣ “ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንን እና የዮዳሄን ልጅ በናያስን ጥሩልኝ” አለ። እነርሱም በንጉሡ ፊት ቀረቡ። 33 ንጉሡም እንዲህ አላቸው፡- የጌታችሁን አገልጋዮች ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤ ልጄን ሰሎምንንም እኔ በምቀመጥባት በቅሎ አስቀምጡትና ወደ ግዮን አውርዱት። 34 ካህኑ ሳዶቅና ነቡዩ ናታን ቀብተው በእስራኤል ላይ ያንግሡትና መለከት በመንፋት “ንጉሥ ሰለሞን ለዘላለም ይኑር!” በሉ። 35 ከዚያም ተከትላችሁት ትመጣላችሁ፣ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል፤ በእኔ ምትክ ይነግሣልና። በእስራኤልና በይሁዳ ላይ እንዲገዛ ሾሜዋለሁ”። 36 የዮዳሄ ልጅ በናያስም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፡- “ይሁን! ይህንንም የጌታዬ የንጉሡ አምላክ ጌታ እግዚአብሔር ያጽናው። 37 ጌታ እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር እንደ ሆነ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን፤ ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሥ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርገው” አለው፡፡ 38 ስለዚህ ካህኑ ሳዶቅ፣ ነቢዩ ናታን፣ የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ ከሊታውያንና ፈሊታውያን ወረዱ፤ ሰሎሞንን በንጉሥ ዳዊት በቅሎ ላይ በማስቀመጥ ወደ ግዮን አመጡት። 39 ካህኑ ሳዶቅ ዘይት ያለበትን ቀንድ ከድንኳን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው። በዚያን ጊዜ መለከት ነፉ፣ ሕዝቡም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን ለዘላለም ይኑር!” አሉ። 40 ሕዝቡም ሁሉ ተከትሎት ወጣ፣ ሕዝቡም እምቢልታ እየነፉ በታላቅ ደስታ ደስ አላቸው፣ ከድምፃቸው የተነሣ ምድር ተንቀጠቀጠች። 41 አዶንያስና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንግዶች ሁሉ ምግባቸውን እንደጨረሱ ይህንን ድምፅ ሰሙ። ኢዮአብ የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ፣ “ይህ በከተማ ውስጥ የሚሰማው ሁካታ ምንድን ነው?” አለ። 42 እርሱ ገና በመናገር ላይ እያለ የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ። አዶንያስም፣ “ና ግባ፤ አንተ ጥሩ ሰው ስለሆንክ መልካም ዜና ይዘህ ሳትመጣ አትቀርም” አለው። 43 ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፡- “ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን እንግሦታል፤ 44 ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካህኑን ሳዶቅን፣ ነቢዩን ናታንን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ ከሊታውያንን እና ፈሊታውያንን ልኳል። እነርሱም ሰለሞንን በንጉሡ በቅሎ ላይ አስቀመጡት። 45 ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታንም በግዮን ቀብተው አነገሡት፤ ደስ እያላቸውም ከዚያ ወጡ፣ በከተማው ሁካታ የሆነው ለዚህ ነው። የሰማችሁት ድምፅም ይኸው ነው። 46 ደግሞም ሰሎሞን በመንግሦቱ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። 47 ከዚህም በላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ባለሟሎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ዳዊት ቀርበው አምላክህ እግዚአብሔር ሰሎሞንን ከአንተ ይበልጥ ዝናውን ያግንነው፣ መንግሥቱንም ይበልጥ ታላቅ ያድርገው ሲሉ አክብሮታቸውን ገልጠዋል፤ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በአልጋው ላይ ሳለ ለእግዚአብሔር ሰገደ፡፡ 48 ዛሬ ከእኔ ዘሮች መካከል አንዱ በእኔ እግር ተተክቶ እንዲነግሥ ያደረገና ይህን ለማየት ያበቃኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ 49 አዶንያስ የጠራቸው ተጋባዦች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ሁሉም ተነሡ፤ እያንዳኑዱም በየፊናው ተበተነ፤ 50 አዶንያስም ሰሎሞንን ስለፈራ ወደ ተቀደሰው ድንኳን ሄዶ የመሠዊያውን ቀንዶች በመያዝ ተማጠነ፡፡ 51 ሰዎቹም ሰሎሞንን፣ አዶንያስ አንተን ከመፍራቱ የተነሣ የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ከሁሉ በፊት ንጉሥ ሰሎሞን የማይገድለኝ መሆኑን በማረጋገጥ በመሐላ ቃል ይግባልኝ በማለት እየተማጠነ ነው ሲሉ ነገሩት፡፡ 52 ንጉሥ ሰሎሞንም መልካም ሰው ከሆነ ከራስ ጠጉሩ አንዲት እንኳን አትነካበትም፤ ክፉ ሆኖ ከተገኘ ግን ይሞታል ሲል መለሰ። 53 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን አዶንያስን ከመሠዊያው አውርደው ያመጡት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፤ አዶንያስ ወደ ንጉሡ ፊት በመቅረብ ወደ መሬት ራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም ወደ ቤትህ ሂድ አለው።