ምዕራፍ 1

1 ከመጀመሪያው ስለ ነበረው፣ ስለ ሰማነው፣ በዓይኖቻች ስላየነው፣ ስለ ተመለከትነው ፣በእጆቻችንም ስለ ዳሰስነው ስለ ህይወት ቃል 2 ህይወትም ተገልጦ ነበር ፤እኛም አይተናል፣ምስክሮችም ነን፤ በአብ ዘንድ ስለ ነበረው ለእኛም ስለ ተገለጠው፣ የዘላለም ሕይወት እንናገራለን፤ 3 ከእኛም ጋር ህብረት እንዲኖራቸሁ፣ ያየነውንና የሰማነውን እንነግራችኋለን፤ ህብረታችንም ከአብና፣ ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው፡፡ 4 ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ፣እነዚህን ነገሮች እንጽፍላችኋለን። 5 ከእርሱ የሰማነው፣ለናንተም የምንነግራችሁ መልዕክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ በእርሱም ምንም ጨለማ የለም፤ የሚል ነው፡፡ 6 ከእርሱ ጋር ህብረት አለን እያልን፣ ነገር ግን በጨለማ ውስጥ ብንመላለስ፣እንዋሻለን ፣እውነትንም አናደርግም፡፡ 7 እርሱ ብርሃን እንደሆነ ፣ በብርሃን ብንመለላለስ እርስ በርሳችን ህብረት ይኖረናል፡፡የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስም ደም ከሃጢአት ሁሉ ያነጻናል። 8 ሃጢያት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። 9 ነገር ግን ሃጢያታችንን ብንናዘዝ፣ሃጢያታችንን ይቅር ሊለንና ከዓመጽ ሁሉ ሊያነጻን፣ የታመነና ፃድቅ ነው፡፡ 10 ሃጢአት አላደረግንም ብንል፣ ሃሰተኛ እናደርገዋለን፣ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም፡፡