ምዕራፍ 1
1
በእግዚአብሔር ፈቃድ ሐዋርያ ሊሆን በክርስቶስ ኢየሱስ የተጠራ ጳውሎስና ወንድማችን ሶስቴንስ በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት።
2
የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት ደግሞ እንጽፍላቸዋለን።
3
ከአባታችን ከእግዚአብሔር ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
4
ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰጣችሁ ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሳ ሁልጊዜ ስለእናንተ አምላኬን አመሰግናለሁ።
5
በነገር ሁሉ፤በንግግርና በዕውቀት ሁሉ ባለጸጋ እንድትሆኑ አድርጎአችኋልና።
6
ስለክርስቶስ የተሰጠው ምስክርነት በመካከላችሁ እውነት ሆኖ እንደጸና ሁሉ ባለጸጎች አድርጎአችኋል።
7
ስለዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጉጉት ስትጠባበቁ አንድም መንፈሳዊ ስጦታ አይጎድልባችሁም።
8
እርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል።
9
ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።
10
ስለዚህ ወንድሞችና እህቶች ሆይ፤ ሁላችሁም በአንድ አሳብ እንድትስማሙ እንጂ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ድርስቶስ ስም አሳስባችኋለሁ። እንዲሁም በአንድ ልብና በአንድ ዓለማ የተባበራችሁ እንድትሆኑ አሳስባችኋለሁ።
11
በመካከላችሁ መከፋፈል እንደተፈጠረ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛል።
12
ይህን የምላችሁ፦ እያንዳንዳችሁ፦ "እኔ ከጳውሎስ ጋር ነኝ፥ ወይም ከአጵሎስ ጋር ነኝ፤ ወይም እኔ ከኬፋ ጋር ነኝ፤ ወይም እኔ ከክርቶስ ጋር ነኝ" ትላላችሁ።
13
ለመሆኑ ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይም የተጠመቃችሁት በጳውሎስስ ስም ነውን?
14
ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ማናችሁንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
15
ስለዚህ ማናችሁም በእኔ ስም እንደተጠመቃችሁ ለመናገር አትችሉም። (የእስጢፋኖስን ቤተ ሰብ ደግሞ አጥምቄአለሁ።
16
ከዚህ ውጪ ሌላ ማንን አጥምቄ እንደሆነ አላውቅም።)
17
ክርስቶስ ወንጌልን እንድሰብክ እንጂ እንዳጥምቅ አላከኝም። በሰው ጥበብ እንድሰብክ አልላከኝም፤ እንዲሁም የክርስቶስ መስቀል ኃይሉ ከንቱ መሆን ስለሌለበት በሰው የንግግር ጥበብ አልሰብክም ።
18
ስለመስቀሉ ያለው መልእክት ለሚጠፉት ሞኝነት፤ ነገር ግን ለምንድን ለእኛ የእግዚአብሔር ኃይል ነው።
19
"የጥበበኖችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የአስተዋዮችንም ማስተዋል ከንቱ አደርጋለሁ" ተብሎ ተጽፎአልና።
20
ጥበበኛ ሰው የት አለ? ፈላስፋስ የት አለ? የዚህ ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?
21
ዓለም በጥበብዋ እግዚአብሔርን ስላላወቀች በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖአል።
22
አይሁድ ታዓምራትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ።
23
እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን። ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለግሪክ ሰዎችም ሞኝነት ነው።
24
ነገር ግን እግዚአብሔር ለጠራቸው ለአይሁዶችም ሆነ ለግሪክ ሰዎች የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ የሆነውን ክርስቶስን እንሰብካለን።
25
ምክንያቱም የእግዚአብሔር ሞኝነት የሚመስለው ነገር ከሰዎች ጥበብ ይበልጣል፤ እንዲሁም የእግዚአብሔር ድካም የሚመስለው ነገር ከሰዎች ብርታት ይበልጣል።
26
ወንድሞችና እህቶች ሆይ፤ በእናንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ጥሪ ተመልከቱ። ብዙዎቻችሁ በሰው መስፈርት ጥበበኞች አልነበራችሁም። ብዙዎቻችሁ ኃያላን አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ከመሳፍንት አልነበራችሁም።
27
ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ። ብርቱንም ነገር ለማሳፈር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ።
28
ዓለም እንደ ከበረ ነገር የምትቆጥረውን ከንቱ ለማድረግ እግዚአብሔ የዓለምን ምናምንቴ ነገር መረጠ። የተናቀውንና ያልሆነውን ነገር መረጠ።
29
ይህን ያደረገው ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመመካት ምክንያት እንዳይኖረው ነው።
30
በክርስቶስ ኢየሱስ ለመሆን የበቃችሁት ከእግዚአብሔር ሥራ የተነሳ ነው፤ እርሱም ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፤ጽድቃችንና ቅድስናችን ቤዛችንም ሆኖአልና።
31
እንግዲህ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ፦"የሚመካ በጌታ ይመካ" ነው።