5

1 የአዳም የትውልድ ሐረግ እንደሚከተለው ነው። እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረው ጊዜ በራሱ አምሳያ ፈጠራቸው፤ 2 ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፣ ባረካቸውም። በተፈጠሩም ጊዜ ‘ሰው’ ብሎ ጠራቸው። 3 አዳም ዕድሜው 130 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እርሱን የሚመስል ወንድ ልጅ ወለደ፣ ስሙንም ‘ሤት’ ብሎ ጠራው። 4 አዳም ሤትን ከወለደ በኋላ 800 ዓመታት ኖረ። ሌሎችን ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ 5 930 ዓመት ሲሆነውም ሞተ። 6 ሤት ዕድሜው 105 ሲሆን ሄኖስን ወለደ። 7 ሄኖስን ከወለደ በኋላ ሤት 807 ዓመት ኖረ። ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 8 ሤት 912 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 9 ሄኖስ 90 ዓመት ሲሆነው ቃይናንን ወለደ። 10 ሄኖስ ቃይናንን ከወለደ በኋላ 815 ዓመታት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 11 ሄኖስ 905 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 12 ቃይናን 70 ዓመት ሲሆነው መላልኤልን ወለደ። 13 ቃይናን መላልኤልን ከወለደ በኋላ 840 ዓመታት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 14 ቃይናን 910 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 15 መላልኤል 65 ዓመት ሲሆነው ያሬድን ወለደ። 16 መላልኤል ያሬድን ከወለደ በኋላ 800 ዓመታት ኖረ። ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 17 መላልኤል 895 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 18 ያሬድ 162 ዓመት ሲሆነው ሄሮክን ወለደ። 19 ያሬድ ሄኖክን ከወለደ በኋላ 800 ዓመታት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 20 ያሬድ 962 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 21 ሄኖክ 65 ዓመት ሲሆነው ማቱሳላን ወለደ። 22 ሄኖክ ማቱሳላን ከወለደ በኋላ የእግዚአብሔርን መንገድ በመከተል 300 ዓመታት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 23 ሄኖክ 365 ዓመታት ኖረ። 24 ሄኖክ የእግዚአብሔርን መንገድ በመከተል ኖረ፣ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለወሰደው አልተገኘም። 25 ማቱሳላ 187 ዓመት ሲሆነው ላሜሕን ወለደ። 26 ማቱሳላ ላሜሕን ከወለደ በኋላ 782 ዓመታት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 27 ማቱሳላ 969 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 28 ላሜሕ 182 ዓመት ሲሆነው አንድ ወንድ ልጅ ወለደ። 29 “ይህ ልጅ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከልፋታችንና ከብርቱ ሥራችን ያሳርፈናል” ሲል ስሙን ‘ኖህ’ ብሎ ጠራው። 30 ላሜሕ ኖህን ከወለደ በኋላ 595 ዓመታት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 31 ላሜሕ 777 ዓመታት ከኖረ በኋላ ሞተ። 32 ኖህ 500 ዓመታት ሲሆነው ሴም፣ ካምንና ያፌትን ወለደ።