3

1 እግዚአብሔር በምድር ላይ ከፈጠራቸው ማናቸውም ሌሎች አራዊቶች ሁሉ ይልቅ እባብ ተንኮለኛ ነበር። እርሱም ሴቲቱን፦ “በእርግጥ እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሎአልን?” ብሎ ጠየቃት። 2 ሴቲቱም ለእባቡ፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት የዛፎች ፍሬዎች መብላት እንችላለን፤ 3 ነገር ግን በአትክልቱ ስፍራ መካከል ስለሚገኘው ዛፍ እግዚአብሔር “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም” ብሎአል። 4 እባብም ለሴቲቱ፦ “በፍጹም አትሞቱም። 5 ከእርሱ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉውን የምታውቁ እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው አላት።” 6 ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት መልካም፣ ሲያዩት ደስ የሚያሰኝና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደሆነ ተመልክታ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷ ጋር ለነበረውም ለባሏ ከፍሬው ሰጠችው፣ እርሱም በላ። 7 የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፣ ራቁታቸውን እንደነበሩም አወቁ። የበለስ ቅጠሎችንም በማጋጠም ከሰፉ በኋላ ለራሳቸው መሸፈኛ ግልድም ሠሩ። 8 ቀኑ ወደ ምሽት ሲቃረብ በአትክልት ስፍራው ሲመላለስ የእግዚአብሔር አምላክን ድምፅ ሰሙ፤ ስለዚህ አዳምና ሚስቱ ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በመሸሽ በአትክልቱ ስፍራ በነበሩት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። 9 እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ጠራውና፣ “የት ነህ?” አለው። 10 አዳምም፣ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ድምፅህን ሰማሁና ራቁቴን ስለነበርሁ ፈራሁ፤ በዚህም ምክንያት ተሸሸግሁ።” 11 እግዚአብሔርም፦ “ራቁትህን እንደሆንክ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ከዛፉ ፍሬ በላህን?” አለው። 12 አዳምም፦ “አብራኝ እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝ፣ እኔም በላሁት” አለ። 13 እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን፦ “ምንድነው ያደረግሽው?” አላት። ሴቲቱም፦ “እባቡ አታለለኝና በላሁ” አለች። 14 እግዚአብሔር አምላክም ለእባቡ፦ “ይህንን በማድረግህ ከእንስሳት ሁሉና ከምድር አራዊት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ትሆናለህ። በደረትህ እየተሳብክ ትሄዳለህ፣ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ አፈር ትበላለህ። 15 በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካካል ጠላትነትን አደርጋለሁ። የእርሷ ዘር ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ተረከዙን ትነክሳለህ” አለው። 16 ለሴቲቱም እንዲህ አላት፦ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በስቃይም ትወልጃለሽ። ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዢሽ ይሆናል።” 17 ለአዳምም እንደዚህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ ‘ከእርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ከዛፉ ፍሬ ስለበላህ ከአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በከባድ ድካም ምግብህን ከእርሷ ታገኛለህ። 18 ምድር እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። 19 ከተገኘህበት አፈር እስክትመለስ ድረስ በላብህ እንጀራን ትበላለህ። አፈር ነህና ወደ አፈር ተመልሰህ ትሄዳለህ”። 20 የሕያዋን ሁሉ እናት በመሆኗ አዳም ለሚስቱ ‘ሔዋን’ የሚል ስም አወጣላት። 21 እግዚአብሔር አምላክ ከቆዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። 22 እግዚአብሔር አምላክ፦ “መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማውቅ ረገድ አሁን ሰው ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖአል። ስለዚህ አሁን እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ቀጥፎ እንዳይበላ ለዘላለምም እንዳይኖር ሊፈቀድለት አይገባም” አለ። 23 በዚህም ምክንያት የተገኘባትን ምድር እንዲያለማ እግዚአብሔር አዳምን ከኤደን የአትክልት ስፍራ አስወጣው። 24 ስለዚህ እግዚአብሔር አዳምን ከአትክልት ስፍራው አባረረው፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ከኤደን የአትክልት ስፍራ በስተቀኝ በኩል ኪሩቤልን እንደዚሁም በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ አኖረ።